ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረው የዲፕሎማሲ ፍሬ

You are currently viewing ፈተናን ወደ ዕድል የቀየረው የዲፕሎማሲ ፍሬ

የተገኘው  ውጤት ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራዊ ትልሞችንም በዲፕሎማሲው ማሳካት እንደምትችል አስተምሯል

                                  በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ተመራማሪ ታምራት ዲና

የዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጣሪ ስጦታ፣ የእምነትና ባህል፣ የሀገራዊ ደህንነት፣ አንድነትና ክብር መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከሚፈስሰው የዓባይ (ናይል) ውሃ 86 በመቶ የሚሆነውን የምታበረክት ቢሆንም ወንዙን በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳታውለው ኖራለች፡፡ ይልቁንም ለም አፈርና ማዕድኗን እየጠራረገ እየወሰደ፤ “ዓባይ ማደሪያ የሌለው…” እየተባለም የእንጉርጉሮና ቁጭት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት የማካሄድ የዘመናት ህልም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፤ ጉባ ወረዳ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል መፈታት ጀመረ፡፡ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በጠንካራ ህዝባዊ ተሳትፎ ታጅቦ፣ በየጊዜው ላጋጠሙ ፈተናዎች መፍትሔዎችን በማበጀት በአሁኑ ወቅት ግንባታው ወደ መገባደዱ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ለህዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ በሚቀጥሉት 6 ወራት ግድቡ ተጠናቅቆ ሪቫን እንደሚቆረጥ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ ሀሳብ፣ ገንዘብና ጉልበት በዓባይ ውሃ ግድብ ለመገንባት ስትነሳ፣ ግብፅ “ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚመጣውን የዓባይ ውሃ ፍሰት በመቀነስ የመስኖ፣ አሳ እርባታ ልማት ስራዎቼ ላይ አደጋ ይደቅንብኛል፡፡ ናይል ስጦታዬ ነው፤ የህልውናዬ መሰረት ነው፤ የውሃ ድርሻዬ መነካት የለበትም” በሚል ግንባታው እንዲጓተት ብሎም እንዲቆም ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር ጥረት ስታደርግ እንደነበር በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት ዲና ይናገራሉ፡፡

ግድቡ እየተፋጠነ ሲመጣም በዲፕሎማሲ፣ ፕሮፖጋንዳና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ስራውን ለማስተጓጎል ጫና እያበረታች መጣች፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም “ጥቅሜን ለማስጠበቅ ማናቸውም አይነት አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸው” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ በሚዲያዎች ስታሰራጭ ነበር፡፡ የግድቡን ደህንነትም በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ በተሳሳተ መልኩ እንዲረዳው ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው ማደናገሪያዎችን ስታነሳ ቆይታለች፡፡ 

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት እንደሚናገሩት፣ በተለይ ግብፅ “ግድቡ የሰላምና ደህንነት ስጋት ይፈጥራል” በሚል ዓለም አቀፋዊ መልክ በማላበስ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክራለች፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን ሀገራትና የዓለም ባንክን ከጎኗ በማሰለፍ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አጀንዳ በማድረግ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ እንዲሰጡበት ጫና አድርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በውሃ ሙሊትና አለቃቀቅ ላይ በአሜሪካ፣ በዓለም ባንክና በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ታዛቢነት የተካሄደው ድርድር ያለ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ በኢትዮጵያ ላይ ፈተናዎች በርትተው ነበር፡፡ “ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ የውሃ ሙሊት መጀመር የለበትም” በሚል ሱዳንና ግብፅ ኢትዮጵያ በውሃው አሞላልና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ተንቀሳቅሰዋል፡፡

አሜሪካ በታዛቢነት በተሳተፈችበት የሶስቱ ሀገራት ድርድርም፣ ከታዛቢነት በመውጣትና የስምምነት ረቂቅ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትፈርም ጫና ያደረገችበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሀዊ የሆነውን ስምምነት ባለመፈረም ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲታይ የሚል ጠንካራ አቋም በመውሰድ ውጤታማ ዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን የውጭ ግንኙነት ተመራማሪው ታምራት ያነሳሉ፡፡

በወቅቱ የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩትና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) መጋቢት 2012 ዓ.ም በወጣው ቁጥር 8 የ“ታላቁ የህዳሴ ግድብ” መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ግብፅ የውሃ ሙሊቱ በተራዘመ ጊዜ በተለይ ድርቅ ካጋጠመ ከ20 ዓመት በላይ ጊዜ እንዲሆን፣ ድርቅ ከተከሰተ ግድቡ ውሃ ሳይሞላ እንዲለቀቅ፣ በውሃ አለቃቀቅ ወቅት ድርቅ በመጣ ቁጥር ውሃ በመልቀቅ የኢትዮጵያ ሀይል የማመንጨት አቅም የተዳከመ እንዲሆን የሚያደርግ ሀሳብ አንስታ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በክረምት ከፍተኛ የውሃ ፍሰት ባለበት ወቅት እንደሚደረግ በማሳወቅ የውሃ ሙሊቱን አከናውናለች፡፡

በሱዳን በኩልም የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሊት ከመከናወኑ በፊት ያልተጨበጡ ስጋቶች በስፋት ተስተጋብተዋል፡፡ “20 ሚሊዮን ሱዳናውያን ችግር ውስጥ ሊወድቁ ነው። ከኢትዮጵያ የሚመጣው የውሃ መጠን በመቀነሱ ከሮዛሪስ ግድብ በታች ያሉ የመጠጥ ውሃ ተቋሞች ውሃ አጥተዋል፤ በርካታ ህዝብም እየተጎዳ ነው” በሚል የሀሰት ክሶች ሲቀርቡ ነበር፡፡

የክረምቱ ወራት ደርሶ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከተጠናቀቀ በኋላ የታየው ግን የሱዳን ስጋት መሰረተ-ቢስ እንደሆነ ነበር፡፡ ግድቡ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ሲሞላ፣ ወደ ሱዳንና ግብፅ የሄደው ውሃ አልቀነሰም ነበር፡፡ እንደውም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የዓባይ ውሃ ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ የነበረበትና ሱዳንም በጎርፍ መጥለቅለቅ የተጠቃችበት ክረምት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡

ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊት ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት ሱዳንና ግብፅ ከመጀመሪያው ዓመት በጠነከረ መልኩ ሙሊቱ እንዳይካሄድ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡

ኢንጂኒዬር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ “በህዳሴ ግድብ ድርድር የግብፅ ድብቅ ፍላጎት፣ ኢትዮጵያ ልትቀበል የማትችለው፣ የራሷንና የሱዳንን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቀውን የ1929 እና የ1959 ውል በተዘዋዋሪ መንገድ ለማስፈፀም መጣር ነው፡፡”

የዲፕሎማሲ ጫናውን እንዴት መመከት ተቻለ?

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ የገጠማትን የዲፕሎማሲ ጫናዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መመከትና ማሸነፍ እንደቻለች ያስረዳሉ። አንደኛ ኢትዮጵያ ሲደረግባት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመመከት “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት” በሚለው መርህ  ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ በፅናት ታግላለች፡፡

ሌላው ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገጠማትን ፈተናዎች መመከትና በአሸናፊነት እንድትወጣ ያደረጋት ከተለያዩ ሀገራት ጋር የፈጠረችው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሆነ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የብዝሃ መደራደር አቅምን በማከማቸት፣ በተለይ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ደጋፊ ሆነው እንዲመጡ ውሃውን በፍትሀዊነትና ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መጠቀም የሚያስችለው የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲተገበር ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርታለች፡፡

ፍትሀዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም የሚያሰፍነውን የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲና የመሳሰሉ ሀገራት የህጋቸው አካል አድርገው አጽድቀውታል፡፡ በሐምሌ 2016 ዓ.ም ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ህግ አድርጋ በመቀበሏ ስምምነቱ ወደ ተግባር እንዲገባና የተፋሰሱ ሀገራት በግዛቶቻቸው ያለው የናይል ውሃ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ እንዲጠቀሙ በር ከፍቷል፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መምህር አበራ ሄብሶ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች፣ ብሔራዊ ህልውናዋ ላይ የሚመጡ አደጋዎችን መመከት የሚችል ተፈጥሯዊ ውቅር ያለው ህዝብ ያለባት ሀገር ናት፡፡ መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ሲነሳም ህዝቡ በሁለንተናዊ መልኩ ለግድቡ ድጋፍ በማድረጉ በግድቡ ግንባታ ሂደት ያጋጠመውን ፈተና መሻገር አስችሏል፡፡

“በዲፕሎማሲ አሸናፊ መሆን የሚቻለው እውነት በመያዝ ብቻ አይቻልም፡፡ ህዝብን ባሳተፍንበት፣ አጋርና ደጋፊዎችን ማሰባሰብ በቻልንበት ልክ ነው፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሂደትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራርና ዲፕሎማቶች፣ ዜጎች የኢትዮጵያን እውነት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዲረዳው ዲፕሎማሲያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል” ይላሉ፡፡

በባለ ሁለትዮሽ ወገን ግንኙነትም በመሪዎች ደረጃ በሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት በተለይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ግብፅ በማቅናት ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ያደረጉት ውይይት ውጤታማ ነበር፡፡ በግብፃውያን ዘንድ “ኢትዮጵያ ውሃን በማቆም ልታስጠማን ነው” የሚለውን በመረጃ ያልተመሰረተ ፕሮፖጋንዳና የተሳሳተ አረዳድ ያከሸፈ እንደነበር የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት ያነሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን ያካተተ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በማዋቀርና ወደ ግብፅ እንዲያቀና በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር የዲፕሎማሲ ጫናውን ማለዘብ አስችሏል፡፡

የድሉ አንድምታ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደ “ሁለተኛው የዓድዋ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው” የሚሉት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው ታምራት፣ ግድቡ ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሯል፤ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ሲቆሙ ምን ማሳካት እንደሚችሉ ያሳየ አመላካች ካርታ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክና ጫናዎች ፊት ለፊት በመጋፈጥ ኢትዮጵያ የመደራደር አቅሟን፣ በራስ መተማመንንና ፅናት ማንፀባረቅ እንድትችል እድል የሰጠ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ሌሎች ሀገራዊ ትልሞችን በዲፕሎማሲ ማሳካት እንደምትችል ያስተማረ እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ታምራት ያነሳሉ፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገኘው ውጤት ከታሪካዊ፣ ህጋዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች አንጻር ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት እንዳለባትና ጉዳዩም አጀንዳ ተደርጎ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ዕድል እየፈጠረ ነው ይላሉ፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review