AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ፊንላንድ በትምህርት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፃለች፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ከፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ጋር ተወይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ፊንላንድ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድርግ የሄደችበት መንገድ በሞዴልነት የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን እና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሪፎርሙ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፣ በትምህርት ዘርፉ የሪፎርም ሥራዎች ድጋፍ የሚያደርጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የትምህርት አጋር ድርጅቶች ገንዘባቸው በትክክል ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በሚያረጋግጥ እና የትምህርት ሚኒስቴርን የሪፎርም እቅዶች ለማሳካት በሚያስችል መልኩ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ በበኩላቸው በትምህርቱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በርካታ ሥራዎችን በትብብር መስራታቸውን ጠቁመው፣ ይህንን ተግባር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚፈልጉ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡