AMN-መስከረም 23/ 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በድምቀት እንዲከበር ከአባ ገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ወቅት በሰው ኃይል፣ በሎጀስቲክስና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዘ በዓሉ ያለምንም ችግር እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የዘመን መለወጫ እና የመስቀል በዓላት በድምቀት ተከብረው እንደተጠናቀቁ ሁሉ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላትም በጥሩ ሁኔታ ተከብረው እንዲጠናቀቁ የአባገዳዎችና የሀደሲንቄዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት ከወዲሁ 24/7 በመሥራት በተካሄዱ ኦፕሬሽኖች የበዓሉን ድባብ ለማጠልሸት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከታጠቁት ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተረናግረዋል፡፡
አባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች በበኩላቸው የፀጥታና ደኅንነት አካላት ላደረጉት ዝግጅት ምስጋና በማቅረብ ጥበቃው የተጠናከረ እንዲሆንና ማንኛውም የበዓሉ ታዳሚ ለፍተሻ ተባባሪ እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከፌደራል ፓሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡