ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በቀጣይ 7 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል-የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች

You are currently viewing ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በቀጣይ 7 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል-የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች

AMN-ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ በቀጣይ 7 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የ2016 ዓ/ም የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን ሪፖርቱን የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ መለሰ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡላቸው ጉዳዮች ቀልጣፋ ውጤታማ እና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ዋነኛ ግብ አድርገው በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ቤቶች ቅልጥፍና መለኪያ የሆነው የመዛግብት ማጣራት ምጣኔን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት በሁሉም ፍርድ ቤቶች ካለፈው ዓመት የዞረና አዲስ የተከፈቱ መዛግብት ቁጥር በጠቅላላው 155 ሺ 323 መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 151 ሺ 405 መዝገቦች እልባት አግኝተዋል ብለዋል፡፡በዚህም የመዛግብት ማጣራት ምጣኔ 98 መቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በይግባኝ እና በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ቀርበው ውሳኔ ያገኙ የፍትኃ ብሄር መዝገቦች 16 ሺ 254 መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 14 ሺ 333ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዳኞች የዳኝነት ስራቸውን ሲያከናወኑ ከአስፈጻሚው አካል፣ ከፍርድ ቤት አመራሮችና ከጎንዮሽ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ ለሚሰጡ ውሳኔዎች ትክክለኛነት ወሳኝ በመሆናቸው ፍርድ ቤቶች ሙሉ በመሉ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መልኩ የዳኝነት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህንንም ከዳኞች ፣ከሰራተኞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ለመለየት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዮች እርካታ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የዳኝነት አገልግሎትን ከብልሹ አሰራር፣ አመለካከትና ተግባር የጸዳ ለማድረግ ዳኞችና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ማቅረብ የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቶ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች መርምሮ ውሳኔ እየሰጠ መሆኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱም የዲስፕሊን ክስ የቀረበባቸው 1 ዳኛ እና 1 የድጋፍ ሰራተኛ ጉዳያቸው ታይቶ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉ ተገልጿል፡፡

የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የአመለካከት የእውቅትና ክህሎት ክፍተት እየለዩ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ልዩ ትኩረት የሚሹ ማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት ለማግኘት ፍርድ ቤት በሚመጡበት ጊዜ ቅድሚያ በመስጠት እንዲስተናደገዱ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፍትህ አካላት በከተማዋ ምክር ቤት አፈጉባኤ ቡዜና አልከድር የሚመራ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ የነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በፍርድ ቤቶች የጉዳዮች ፍሰት በተመሳሳይ በመጨመር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ጥራት ያለውና ተደራሽ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

የዳኞችን ያለመከሰስ መብት፣ ጥቅማጥቅም ፣እረፍት ፣ ሹመት እና ስንብትን ግልጽ በሆነ ሂደት ለመወሰን የሚያስቸል እና የዳኞችና የተቋሙን መብት የሚያስጠብቅ የዳኞች አስተዳደር አዋጅ ረቂቅ ህግ መዘጋጀቱ ተመላክቷል፡፡

ዋነኛ የሪፎርም ስራ የሆነው የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ለማዘመን የሚያስችል የቴክኖሎጂ መሰረተልማት ስራ በቀጣይ 7 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በቀጣይም ውጤታማና ጥራት ያለው የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እና የሙስናና ሌሎች የስነምግባር ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ተግባራትን በመስራት የክትትልና ድጋፍ ስርዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ መለሰ ያቀረቡት ሪፖርት የምክር ቤት አባላቱ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ በምክር ቤት አባላቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በሰፊና ሁሴን

#Addisababa

#Ethiopia

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review