ፍቱን መድሐኒት የሚሻው የእግር ኳሳችን

You are currently viewing ፍቱን መድሐኒት የሚሻው የእግር ኳሳችን

ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ መድረክ የበይ ተመልካች ከሆነች ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በስፖርቱ ዕድገት ተስፋ ያልቆረጠው የስፖርቱ ደጋፊም ጭላንጭል ተስፋ እንኳን እያሳየ ያልሆነውን እግር ኳስ ከመደገፍ አልቦዘነም፡፡ በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ፊተኛ የነበረችውና በአህጉሪቱ ሯሷ በፈጠረችው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ሳይቀር ጭራ ከሆነች ቆይታለች፡፡

የእግር ኳሱ ችግር ምንድን ነው? አሁንስ ተስፋው በማን ላይ ነው? ኢትዮጵያ ከመሰረተችው አህጉራዊና ከቀጣናዊ ውድድር ለምን ራቀች? እንደዚሁም ከዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪክስ ለምን አልኖራትም? የሚሉት ጥያቄዎችም አሁንም ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ በጠረጴዛው ላይ ይገኛሉ፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችም ለእነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች መፍትሄ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች ከመሰንዘር ቦዝነው አያውቁም፡፡ ይሁንና የልብ የሚያደርስ መፍትሄ አልተገኘም፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም በዚሁ ጉዳይ ላይ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩን ጠቢቡ ሰለሞንን እና በአዲስ አበባ አዳጊ ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት የኢትዮ ዩናይትድ እግር ኳስ አካዳሚ መስራችና አሰልጣኝ ብዙነህ ጽጌን አነጋግሯል፡፡

በአፍሪካ አህጉር የእግር ኳስ ታሪክ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም በዘመናት መካከል እንዳይደበዝዝ ሆኖ በታሪክ ማኅደር ውስጥ ቢሰፍርም ወቅቱን የሚመጥን ዘመናዊ የእግር ኳስ ቡድንን መመሥረት ግን የአጀማመሩን ያህል ቀላል አልሆነም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክያቶች አሉ ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ በየትኛውም ዓለም ላይ እግር ኳስ ትልቅ የቢዝነስ ተቋም መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እግር ኳስ በትክክለኛ ባለሙያዎች ስለማይመራ፣ የአሰለጣጠን ችግር ስላለበት፣ በአካዳሚዎች ግንባታ ላይ ስለማያተኩር፣ አዳጊዎች ላይ ስለማይሰራ እና በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች እግር ኳሱ የታመመ ነው፤ ጠንከር ያለ ህክምና ይፈልጋል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ እግር ኳስን ቀድማ የጀመረችው ኢትዮጵያ በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለቦች ውድድር በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገራት ጋር እንኳን መፎካከር አለመቻሏ በእጅጉ አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልጹት የባህር ዳር ዩንቨርሲቲ መምህሩ አቶ ጠቢቡ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው እግር ኳሱ ላይ ከመሠረቱ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ሳንሰራ እና በእግር ኳሳችንም ውጤታማ ሳንሆን ለዘርፉ የሚወጣውን ወጭ የተጋነነ ማድረጋችን ላይ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን የእርሳቸውን አስተያየት በአሜሪካ ታውሶን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን የደመወዝ አከፋፈል አስመልክቶ ካደረጉት ጥናት ካስደገፍነው ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ 

መምህር ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) በጥናት አረጋግጬዋለሁ እንዳሉት በፕሪሚየር ሊጉ የአንድ ተጫዋች ወርሃዊ ደመወዝ በአማካይ 130 ሺህ ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ የባለሙያው ጥናት በአማካይ የተሰላ ስለሆነ እንጂ በርካታ የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች በወር ከ300 ሺህ ብር በላይ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ በ16ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት በ2016 የበጀት ዓመት ብቻ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው መግለጹን ስንጨምርበት ጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚፈልግ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ይህ የኪሳራ ሪፖርት ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳ እጦት ምክንያት ከአገር አገር እየተዘዋወረ በመጫወቱ ብቻ የመጣ ኪሳራ መሆኑንም ልብ ይሏል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ በርካታ ክለቦች ለተጫዋቾች ደመወዝ ከሚያወጡት ወጪ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ የመፍረስ አደጋ ሲደቀንባቸው ማየትም የተለመደ ነው፡፡  አብዛኛዎቹ ክለቦች ወጪ እንጂ ገቢ ስለማያመነጩ ህልውናቸው አደጋ ላይ ወድቆም ይታያሉ የሚሉት የኢትዮ ዩናይትድ እግር ኳስ አካዳሚ መስራችና አሰልጣኝ ብዙነህ ጽጌም በመምህር ጠቢቡ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ እንደሳቸው አስተያየት ከሆነም ገቢ አለማመንጨታቸው ብቻም ሳይሆን ይህን ያህል ገንዘብ ውጪ እየተደረገ ያለውም በተገቢው ቦታ አለመሆኑ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡

በዶክተር ጋሻው ጥናት መሠረትም 16ቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊዎች ለደመወዝና ጥቅማጥቅም ብቻ በዓመት በአማካይ እያንዳንዳቸው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጡ ተጠቁሟል፡፡ ጥናቱ ይህንን ቢያሳይም የክለቦቹ ወጪ ግን ከዚህም እንደሚበልጥ የስፖርቱ ቤተሰቦች ግምት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ወጪ የሚፈስበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በውጤት ሲመዘን እጅግ ደካማ ተብሎ የሚፈረጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የዚሁ ሊግ ውጤት በመሆኑ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ ከግርጌ የሚገኝ ሆኗል፡፡ የቅርብ ጊዜ ውጤቶችንም ብንመለከት ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው ብሔራዊ ቡድኑ በሁሉም የምድብ ጨዋታዎች ሽንፈትን ማስረናገዱ ተጠቃሽ ነው። በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ዋናው የኢትዮጵያ የወንዶች ብሔራዊ ቡድንም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ሲሸነፍ፣ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል። በጊኒ አቻውም አራት ለአንድ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡

በእርግጥ የእግር ኳሱ ህመም ከገንዘብ አወጣጥ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን ሁለንተናዊ እንደሆነም ባለሙያዎች አልሸሸጉም፡፡ በመሆኑም ችግሩ መፈለግ ያለበት ሁሉም ቦታ እንደሆነና በተለይም የሚዲያ አካላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች፣ መንግሥት እና ሌሎችም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሌላም በኩል አንድ አገር ገጽታ ግንባታ ወሳኝ ከሆኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል የእግር ኳስ ስፖርት ተጠቃሽ ነው፡፡ አዳጊ ወጣቶች ላይ አተኩሮ መስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብም ሆነ የእግር ኳስ ስፖርቱን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለውና ይህ እድል ለኳሱ ዕድገት የማይናቅ ድርሻ እንዳለው ያስረዳሉ አሰልጣኝ ብዙነህ፡፡ እግር ኳሱን ከአንድ ሁነትና ከመሸናነፍ በላይም የኢኮኖሚ ምንጭ እና የብሔራዊ አንድነት መገንቢያ ያደረጉት አገራትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

እግር ኳሱ ከታች መሰረት መያዝ አለበት የሚሉት መምህር ጠቢቡ እግር ኳስ በአራት መሰረታዊ ምሰሶዎች የቆመ ነው፤ ውጤታማ ቡድን የሚገነባው ታክቲክ፣ ቴክኒክ፣ በአካል ብቃት እና በስነ ልቦና ከታች ጀምሮ ሲሰራበት ነው ይላሉ፡፡ በእግር ኳስ የተካነ አዳጊ ለማፍራት ከሦስት እስከ 17 ዓመቱ በአምስት ደረጃዎች ተከፍለው የሚሰጡትን የእግር ኳስ መሰረታዊያን ማግኘት አለበት ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል። ከህጻንነታቸው አንስቶ “ፕሮፌሽናል” የሆኑ ስልጠና ከወሰዱ የሌላ አገራት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን እና ካደጉ በኋላ የኳስ ክህሎት አስተምረን የምናሰልፋቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በሰፋ የጎል ልዩነት ቢሸነፉ ምኑ ያስገርማል? ሲሉም ያነሳሉ፡፡

የአህጉረ አፍሪካ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ከሌሎች ዓለማት ጋር ሲነፃፀር ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ከታዳጊ ስፖርት ማዕከላት ውጤታማነት አንጻር የምዕራብ አፍሪካ አገራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚሁ የአህጉሪቱ አካባቢዎች በሺዎች በሚቆጠሩ አካዳሚዎችን ከመስራታቸው ጎን ለጎን በየሰፈሩ ያሉ የታዳጊ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመስራቱ ረገድ የተሻለ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ አንድ ብላ ከእነዚህ አገራት ልምድ ልትቀስም እንደሚገባም አሰልጣኝ ብዙነህ ጽጌ  ይመክራሉ፡፡

ችሎታ ያላቸው አዳጊ ወጣቶች በሳይንሳዊ ስልጠና ከታገዙ ክለቦችንና ብሔራዊ ቡድንን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የሚሉት ደግሞ የስፖርት ትምህርት ክፍል መምህሩ አቶ ጠቢቡ ሰለሞን ናቸው። ለታዳጊዎች ገና በለጋ ዕድሜያቸው በስነ ምግብ ባለሙያ፣ በአሰልጣኞች፣ በአካል ብቃት ባለሙያዎች፣ በስነ ልቦና ባለሙያዎች ተመጥኖና እየተመዘገበ በስልጠና ወቅት እየታየ የጎደለውን በልምምድ የሚያሳትፍ ስርዓት ቢዘረጋ የስፖርቱን ትንሳኤ ማብሰር ይቸላልም ባይ ናቸው፡፡

በጥቅሉ እንደባለሙያዎቹ አስተያየት ከአንድ ሰሞን ያዝ ለቀቅ ወጥቶ በአገሪቱ የትኛውም ጥግ የወጣቶች ማዕከላት ተቋቁመው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡ አያይዘውም የይድረስ ይድረስ አሰራር ወጥተው አዳጊዎቹ እግር ኳስ ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ የአካል ብቃት፣ ስነ ልቦና ዙሪያ ሳይንሱን በተከተለ መልኩ ለመስራት ይኖርባቸዋል በማለት አብራርተዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review