ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የካድፕ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው

AMN – ጥር 3/2017 ዓ.ም

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በመሪዎች ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካድፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዩጋንዳ ካምፓላ እየተደረገ የሚገኘው አስቸኳይ ስብስባ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

የዛሬው ስብሰባ በመሪዎች ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ የኮሚሽኑ የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ እና ሌሎች የህብረቱ አመራሮች፣የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የግብርና ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ፣ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው በስብሰባው ላይ እየሳተፉ ይገኛል።

በስብሰባው የካድፕ ያለፉት 10 ዓመታት አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን፤ በፈረንጆቹ ከ2026 እስከ 2035 የሚተገበረው የካድፕ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

ዘላቂ የምግብ ምርታማነት፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ የዜጎች ተጠቃሚነት፣ የማይበገር የምግብ ስርዓትን ግንባታ እና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ውይይት ከሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የመሪዎቹ ስብስባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዴፕ) የአጀንዳ 2063 አህጉራዊ ማዕቀፍ ሲሆን የአፍሪካ አገራት በግብርና መር ልማት አኮኖሚያቸውን በማሳደግ ረሃብን እንዲያስወግዱ እና ድህነትን እንዲቀንሱ ማድረግ ዋንኛ አላማው ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review