የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከታሪፍ ውጪ ናቸው ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ፣ በስማርት ስልኮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ላይ አዲስ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል፡፡
ቻይና ሰራሽ የሆኑ ስማርት ስልኮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ከቀረጥ ውጪ ሳይሆን በተለየ የታሪፍ መደብ ውስጥ መቀመጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ቻይና በበኩሏ፣ ዶናልድ ትራምፕ በታሪፍ ላይ የተመሰረተ አስተዳደራቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲሰርዙ እና ወደ ትክክለኛው የጋራ መከባበር መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርባለች።
የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር የሆኑት ሃዋርድ ሉትኒክ፣ አዲሱ ቅጣት አሜሪካ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በዓለም በርካታ ሀገራ ላይ ከጣለችው እና ለ90 ቀናት ያዝ ከደረገችው ቀረጥ ተጨማሪ መሆኑን አመላክተዋል።
አክለውም የኛ መድኃኒቶች፣ ከፊል አስተኔዎች (ሰሚኮንዳክተርስ) እና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በአሜሪካ ውስጥ እንዲመረቱ እንፈልጋለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከትናንት በስቲያ፣ የአሜሪካ ጉምሩክ ባወጣው ማስታወቂያ፣ ከቻይና ወደ ሀገሪቱ የሚገቡት ሸቀጦች እንደ ስማርትስልኮች፣ ኮምፒውተሮች እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ከ125 በመቶ ቀረጥ ውጪ ናቸው ማለቱ አይዘነጋም።
በታምራት ቢሻው