AMN-ጥር 13/2017 ዓ.ም
ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት ፣ አሜሪካን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲሁም ከዓለም ጤና ድርጅት ዓባልነት ማስወጣትን ጨምሮ 78 መመሪያዎችን ፈርመዋል፡፡
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ዓባልነት እንድትወጣ የሚያዘው መመሪያ ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያ ቀን ከፈረሙት መመሪያ ቀዳሚው ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሌላኛው በቀዳሚነት ከፈረሟቸው መመሪያዎች መካከል ተጠቃሹ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ከአሜሪካ ለማስወጣት የሚያዘው መመሪያ ነው፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በአስተዳደር ዘመናቸው ቅድሚያ ለመፈጸም ቃል የገቧቸውን ቁልፍ ጉዳዮች እንደሚፈጽሙ ለደጋፊዎቻቸው ባረጋገጡት መሰረትም፣ በፈረንጆቹ ጥር 6 ቀን 2021 በካፒቶል ከተፈፀመ ጥቃት ጋር በተያያዘ ክስ ለተመሰረተባቸው እና ለተፈረደባቸው ወደ 1 ሺህ 600 ለሚሆኑ ሰዎች ይቅርታ የሚያደርገውን ሰነድ ፈርመዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ሁለት ፆታዎች “ወንድ እና ሴት ብቻ ናቸው” የሚለውን ሰነድም ፈርመዋል።
ይህ ውሳኔያቸው ፓስፖርት እና ቪዛ ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት ግንኙነት፣ የሲቪል መብት ጥበቃዎችን፣ የፌዴራል በጀት ጉዳይ እና እስር ቤቶችን የሚመለከት ይሆናል።
በሌላ ትዕዛዝ ደግሞ “ብዝሀነት፣ እኩልነት እና አካታችነት” አሊያም ዲኢአይ እየተባለ የሚጠራውን ፖሊሲ መሻራቸውንም አስታውቀዋል።
የስደተኞች ልጆች ሆነው በአሜሪካ የተወለዱ ህፃናት ዜግነት እንዳያገኙ የሚከለክለውን መመሪያም ፈርመዋል፡፡
የብኩርና መብት (jus soli) በመባል የሚታወቀው የወላጆቻቸው ዜግነት ወይም የኢሚግሬሽን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በአሜሪካ ግዛት ውስጥ ለተወለዱ ዜግነት የሚሰጥ ህጋዊ መርህ ነው።
በሀገሪቱ ውስጥ በ14ኛው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ መሠረት ይህ ልማድ የተጠበቀ ሲሆን፣ ይህም በአሜሪካ ውስጥ የተወለዱ ወይም ዜግነት የተሰጣቸው ሰዎች ሙሉ ዜጋ እንደሆኑ ይደነግጋል።
ይህ ፖሊሲ በኢሚግሬሽን እና በብሔራዊ ማንነት ላይ ለሚካሔድ ክርክር ወሳኝ ሚና እንዳለው ይነገርለታል።
ፕሬዚዳንቱ አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በሽብር ቡድን ማካተትን ጨምሮ በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ ሜክሲኮአዊ ያልሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች የፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኙ በሜክሲኮ እንዲቆዩ የሚያስገድደው ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርገውን መመሪያም ፈርመዋል፡፡
የድንበር ደህንነትን ይበልጥ ከማስጠበቅ አኳያ፣ በቀደመው የስልጣን ዘመናቸው ጀምረውት የነበረው እና ሀገራቸው ከሜክሲኮ በምትዋሰንበት ድንበር ግንብ እንዲገነባ የሚያዘው ሰነድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከፈረሟቸው መመሪያዎች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ፍሪ ፕሬስ ጆርናል ዘግቧል።