መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ጉባኤ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል። ለመሆኑ ላለፉት ስድስት ዓመት በርዕሰ ብሔርነት ያገለገሉትን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ተክተው አዲስ የተሾሙት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ማን ናቸው?
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተወለዱት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል። እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ላንክስተር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በስትራቴጂ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። በተለያዩ ሀገራት በሰላም፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በፖለቲካ ሳይንስ አጫጭር ሥልጠናዎችን እና ኮርሶችን ወስደዋል።
5ኛው ርዕሰ ብሔር ታዬ አፅቀሥላሴ ለበርካታ ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያየ የስራ ኃላፊነት ረዘም ላለ ጊዜ ተመድበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ መምሪያ የሥራ ክፍል፣ የምዕራብ አውሮፓ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ በስቶክሆልም የኢፌዴሪ ኤምባሲ በአማካሪነት፣ በዋሽንግተን የኢፌዴሪ ኤምባሲ በአማካሪነት፣ በሎስ አንጀለስ ቆንስላ ጀነራል፣ በ1998 ዓ.ም ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው ሰርተዋል።

በሎስ አንጀለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ማዕረግ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ በአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል፣ በ2008 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል።
በአሜሪካ፣ በስዊድንና በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ በኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሀገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል። በወቅቱም የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች እና ስብሰባዎች ኢትዮጵያን በመወከል የሀገራቸውን አቋምና ጥቅም ለማስጠበቅ ሰርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሙያ አጋሮቻቸው
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴን በቅርብ ከሚያውቋቸው አንጋፋ ዲፕሎማቶች መካከል አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ አንዱ ናቸው። አምባሳደር ኢብራሂም በዲፕሎማሲው መስክ የካበተ ልምድ ያላቸውና በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ ናቸው፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ቡድን አባል በመሆንም ሰርተዋል፡፡
የአዲሱን ፕሬዝዳንት አገልጋይነትና ብቃትን ሲገልፁም፣ “ሀሳብን በትክክል ለሚፈለገው መድረክ የሚያቀርብ ሰው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ፕሬዝዳንት ታዬ በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን አቋም በማንፀባረቅ የነበራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ የኢትዮጵያን፣ የተደራዳሪዎችን አቋም (በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር) በሰፊውና ግልፅ በሆነ መንገድ አስረድተዋል፤ አሳምነዋል።” ብለዋል፡፡
አዲሱን ፕሬዝዳንት ከሚያውቋቸው ሰዎች መካከል ሌላኛው በዲፕሎማሲው መስክ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ያገለገሉት ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ናቸው፡፡ አምባሳደር ታዬ ጥራት ያለው ሀሳብ ያላቸው፣ ጠንካራ ሰራተኛ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም እና ከሰዎች ጋር ጥሩ የመግባባት ክህሎት ያላቸው፣ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ውጤታማ በመሆን የሚታወቁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር ወደ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ከተወሰደ በኋላ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚለው መርህ መሰረት በአፍሪካ ህብረት በኩል መፍትሔ እንዲያገኝ በብርቱ ተከራክረዋል፡፡ በተለይም ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ሆነው በተሾሙበት ወቅት የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት ያሳዩት ብቃት እና የመጣው ውጤት በጣም የሚያኮራ እንደሆነ አምባሳደር ጥሩነህ ያነሳሉ፡፡
“በፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ጉዳይ የቆየ ድርድር ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ወዳጅ ማፍራትና ከጎን እንዲቆም ማድረግ ነው ትልቅ ውጤት የሚያስገኘው፡፡ በዚህ ረገድ አምባሳደር ታዬ ሩስያ እና ቻይና ከጎናችን እንዲቆሙ በሚደረገው ጥረት ከሀገራቱ ጋር በቅርበት ሰርተዋል፡፡” ብለዋል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በተወያየበት መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ የነበሩት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ታዬ፤ በወቅቱ ካደረጓቸው ንግግሮች፣ “ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት መስራች ሀገር እንደመሆኗ ለተባበሩት መንግስታት ቻርተር መከበር ያላት መርህና ዓላማ ጠንካራና የማይለዋወጥ ነው፡፡ ሁሌም የጋራ ሰላምን፣ ደህንነትንና ባለብዙ ወገን ግንኙነትን ትደግፋለች፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ የየትኛውም ሀገር ስጋት ሆና አታውቅም፡፡ በግልፅ እንነጋገር ከተባለ ዛሬ እየተወያየን ያለንበት ጉዳይ [ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ] በፀጥታው ምክር ቤት ማቅረብ ትክክለኛ ቦታው አይደለም፡፡ ወደፊትም እንዲህ ዓይነት መጥፎ አካሄዶች እንዲቀጥሉ መነሻ የሚሆን እና ለችግሮች መባባስ በር የሚከፍት ነው፡፡” በማለት ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ ማምጣት ተገቢነት እንደሌለው ያነሱበት የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ያላቸውን ልዩነት መፍታት ባይችሉ እንኳን፣ የሶስቱ መሪዎች የተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት አለመግባባቶች በምን መልኩ መፈታት እንዳለበት አካሄዶችን አስቀምጧል፡፡ ከዚህም ባለፈ ልዩነቶችን ለመፍታትና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መፍትሔ ላይ ለመድረስ የአፍሪካ ህብረት በጎ ፈቃድ እና አቅም ያለው መሆኑንም ሞግተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሻገር በተለያዩ መድረኮች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ እውነታውን በማሳወቅ ረገድ በብዙ ጥረዋል። በተለይ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በተጠራው 77ኛው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በቀረበባት የሀሰት ውንጀላ ዙሪያ በተፈቀደላቸው ሁለት ደቂቃ ውስጥ የሰጡት አስደናቂ ምላሽ በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ ነው፡፡
በተመድ የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን ሲሰጡት የነበረውን አገልግሎት አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱም ምስጋና እና እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ “ኢትዮጵያን ማገልገል ትልቅ ክብር እና መታደል ነው” በማለት ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ እንዲወክሉ ለተሰጣቸው ዕድል ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡
አምባሳደር ጥሩነህ እንደሚሉት፣ ፕሬዝዳንት ታዬ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ በነበሩበት ወቅት ካደረጉት አስተዋፅኦ ባሻገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሲያደርጓቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች፣ ሲያቀርቧቸው የነበሩ ሀሳቦች፣ የስራ ቁርጠኝነታቸውን እና ውጤታማ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ርዕሰ ብሔር ባለፉት 4 አስርት ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክ ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በታላቅ ቅንነት፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን ለዚህም የረጅም ዘመን የመንግሥት ሰራተኛ አገልግሎት የክብር የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ