AMN – ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ የኤደንብራ ደቸስ ልዕልት ሶፊ ሔለን ጆንስን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ልዕልቷ ከእንግሊዝ ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ፕሬዝዳንት የተላከውን የደስታ መግለጫ መልዕክት አድርሰዋል።
እንዲሁም ፕሬዝዳንቱ ለልዕልቷ በወቅታዊ አገራዊ፣ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ ከአሁን በፊት በጄኔቫ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ በጋራ ለማሰባሰብ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የእንግሊዝ መንግሥት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ፕሬዝዳንቱ በ79ኛው የ.ተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎንም ከአዲሱ የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መመክራቸውን አስታውሰዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት የገቡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ልዕልት ሶፊ ሔለን ጆንስ በበኩላቸው፣ አሁን ላይ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በዩክሬን እና መካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮሩ ለተቀረው አካባቢ የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ መቀነሱን ገልጸዋል።
አገራቸው በሌሎች አካባቢዎች ለሚያስፈልጉ ሰብአዊ ድጋፎች እንዲጠናከር በሚደረገው ርብርብ የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ ገልጸዋል።
ሁለቱ አካላት በኢትዮጵያ የእናቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና፣የአይነሥውርነትን ለማስቀረት እንዲሁም በግጭት ወቅት ለሚደርስ ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ዙሪያም መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።