ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ወደ ማህበረሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN – ጥር 5/2017 ዓ.ም

የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመግዛት እና በመሸጥ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ወደ ማህበረሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩ 7 ግለሰቦች ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው መቀጠሉን የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ማራቶን ህንጻ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው።

ፖሊስ በቦታው ቁጥጥር በሚያደርግበት ሰዓት በገበያ ቦታዎች ሁለት ግለሰቦች አትክልት እና ፍራፍሬ ግብይት ሲያደርጉ በመጠራጠር ባደረገው ፍተሻ 14 ሺ 6 መቶ ሀሰተኛ ብር እንደተገኘባቸው ተገልጿል።

በዚህም መነሻነት ባደረገው ምርመራ የማስፋት ስራ እና በሌላ አንድ ተጠርጣሪ ላይ በተደረገ አካላዊ ፍተሻ 18 ሺ 6 መቶ ሀሰተኛ ብር መያዙንም ነው የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያስታወቀው።

የወንጀሉን ምንጭ ለማወቅም ፖሊስ ምርመራ በማስፋት የፍ/ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት በዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ላይ ባደረገው ብርበራ በአጠቃላይ 50ሺ ሁለት መቶ ሀሰተኛ ብር እና 7 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም የተያዘውን ኤግዚቢት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሾላ ቅርንጫፍ በመውሰድ ሀሰተኛ መሆኑን የማረጋገጥ ስራ እንደተሰራ እና እንዲወገድ መደረጉንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ወደ ፊትም ህገ ወጥ ተግባራትን እና መሰል ወንጀሎችን የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ማህበረሰቡ እንደዚህ ዓይነት አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እና ትብብር የማድረግ የተለመደ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፏል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review