AMN-የካቲት 19/2017 ዓ.ም
በሀንጋሪ ሁለት ወይም ሶስት ልጆች ያሏቸው እናቶች ለዕድሜ ልክ የገቢ ግብር ከመክፈል ነፃ ይሆናሉ ሲሉ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን አስታውቀዋል፡፡
ውሳኔው ትልቅ ማበረታቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ተጨማሪ ልጆች ለመውለድ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
በአውሮፓ የወሊድ መጠን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2024 የነበረው የወሊድ ምጣኔ በአንድ እናት 1 ነጥብ 43 ብቻ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከእስከ አሁኑ በእጅጉ ያነሰ እንደነበር ተመላክቷል።
በኖርዌይ በፈረንጆቹ 2023 የነበረው የወሊድ ምጣኔ በአንድ እናት 1 ነጥብ 4 ልጆች ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ቁጥሩ ተተመሳሳይ እንደነበር ተገልጿል።
በአህጉሪቱ የተረጋጋ የሕዝብ ቁጥር መጠን እንዲኖር ተተኪ ትውልድ የማፍራት ምጣኔ ደረጃ በእያንዳንዱ እናት 2 ነጥብ 1 ልጆች መሆኑ ተጠቁሟል።
ይሁን እንጂ በመላው አውሮፓ ባሉ ሀገራት ተተኪ ትውልድ የማፍራት ምጣኔ ከተቀመጠው ደረጃ በታች እንደሆነ እና ይህም የሕዝብ ቁጥር እያሽቆለቆለ መሄዱን እንደሚያመላክት ተነግሯል።
ይህ ትልቅ ችግር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሁኔታ ካልተስተካከለ አውሮፓ ወደፊት በግልፅ ትጠፋለች ማለት ነው ሲሉ አክለዋል።
ለዚህም የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ አውሮፓን ዳግመኛ ታላቅ ለማድረግ የወሊድ መጠንን መጨመር እንደሚያስፈልግ እና ይህን ለማድረግም ሴቶች ልጆች እንዲወልዱ ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ በሀንጋሪ እናቶች ሁለት ወይም ሶስት ልጆች የሚወልዱ ከሆነ ለዕድሜ ልክ የገቢ ግብር ከመክፈል ነፃ እንደሚሆኑ ማስታወቃቸውን ዘ ቡዳፔስት ታይምስ ዘግቧል፡፡