ወይዘሮ የሺመቤት ወልደሰንበት ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ አምቦ ዙሪያ በሚገኝ ገጠራማ ሥፍራ ነው። በሕጻንነት ዕድሜያቸው 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለውን መንገድ በየቀኑ ጠዋትና ማታ በእግራቸው ተጉዘውና አራት ወንዞችን ተሻግረው አምቦ ከተማ ተምረዋል። በመቀጠልም በመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ተቀጥረው ከ13 ዓመት በላይ አገልግለዋል። በ1987 ዓ.ም. በዝውውር ወደ አዲስ አበባ ተቀየሩ፡፡
አዲስ አበባ መጥተው እራሳቸውን ካስተካከሉ በኋላ ከልጅነታቸው ጀምሮ በውስጣቸው ተቀብሮ የቆየውን የተቸገረ ሰው የመርዳት ውስጣዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወደሥራ መግባት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ ሥራውን የጀመሩት ስታዲየም አካባቢ በመሄድ ጎዳና ላይ የሚውሉና የሚያድሩ ልጆችን በማፈላለግ ነበር፡፡ ይህንን ችግረኛ ህፃናትን የማሰባሰብ ተግባር ውጤታማ ለማድረግ መንገድ ላይ ተቀምጣ ሶፍትና ማስቲካ የምትሸጥ እህት ትልቅ እገዛ እንዳደረገችላቸው ያስታውሳሉ፡፡ ስታዲየም ላይ ሊጀምሩ የቻሉት በወቅቱ የስራ ቦታቸው ሜክሲኮ ስለነበረ ከቦሌ ሚካኤል ተነስተው ሜክሲኮ ለመድረስ ታክሲ ይይዙ የነበረው ስቴዲየም ስለነበረ ነው፡፡
በዚህች እህት አማካኝነት ቁጥራቸው ስድስት የሚሆኑ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ልጆችን እንዳገኙ ወይዘሮ የሺመቤት ይናገራሉ፡፡ እነዚህን ልጆች ከልመናና ከጎዳና ኑሮ እንዲወጡ ቀርበው ምክር ከመስጠት ጀምሮ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ሃሳብ አንስተው አወያዩዋቸው። “ላስተምራችሁ፣ ፍላጎታችሁን ንገሩኝና ስራ ልፍጠርላችሁ” የሚል ሐሳብም አነሱላቸው፡፡ ህፃናትና አዳጊዎቹም በምላሻቸው፤ “ሦስቱ ጫማ እናጽዳ (ሊስትሮ ሥራ እንስራ) ሌሎች ሦስቱ ደግሞ ሶፍት እያዞርን እንሽጥ” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውና በፍላጎታቸው መሰረት መሥራት የሚችሉበትን አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዳሞሉላቸው ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ የሺመቤት ለእነዚህ ልጆች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ከማድረግ በተጨማሪ፤ በበዓላት ወቅት ከቤታቸው ምግብ ሰርተው የተሰማሩበት ቦታ ድረስ ሄደው ይመግቧቸው ነበር፡፡ ልብስና ጫማ ገዝተው ይሰጧቸውም ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በመሰል ሕይወት ውስጥ እያለፉ ያሉ ልጆችን ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ ሥራውን በስፋት ከመጀመራቸው በፊት ግን ፍቃድ ማውጣት እንዳለባቸው ሰዎች ምክር ሰጧቸው፡፡ ምክሩንም በመቀበል በወቅቱ ፍቃድ ወደሚሰጠው አካል ሄዱ።
ፈቃድ ለማውጣት ባደረጉት ሂደት የተቀጠሩበትን መደበኛ የመንግስት ሥራቸውን እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎታቸውን በአንድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ለማከናወን ቢጥሩም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ከተማ ላይ በርካታ ረጂ ተቋማት ስለነበሩ በሚፈልጉት ልክ መስራት ባለመቻላቸው እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ የህይወት ጥሪያቸውና የልጅነት ህልማቸው በችግር ውስጥ ያሉ ልጆችን የመርዳት ሥራ በመሆኑ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ ወደሆነችው ሆለታ ከተማ ተመላልሰው ለመስራት ወሰኑ። በዚች ከተማ ሥራቸውን መጀመር የሚያስችላቸውን ፍቃድ በ1999 ዓ.ም. አገኙ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም የሚሠሩበት ቦታም እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡
በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችን የሚመለከተው መንግስታዊ ተቋም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና የወረዳው ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን መልምለው አመጡላቸው፤ በወቅቱም ለ42 ህጻናት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ድጋፍ ማድረግ ጀመሩ፡፡ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን፣ አልባሳት፣ ዘይትና ዱቄት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ልጆቹ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉትም የተለያዩ የመንግስት ተቋማትን፣ የግል ድርጅቶችንና ባለሀብቶችን ድጋፍ በመጠየቅ ነው። በ2001 ዓ.ም. የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተው ያገኙትን ገንዘብ እና የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት በሰጣቸው የማበረታቻ ገንዘብ የሆለታ ከንቲባ በሰጣቸው መሬት ላይ ለቢሮና ለመጋዘን አገልግሎት የሚውል ሁለት ክፍል ቤት መሥራት መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህንን የበጎነት ተግባር አምቦ ከተማ ላይም መጀመር ቻሉ፡፡
በሂደት ሁለቱንም ማለትም ተቀጥረው ይሠሩበት ከነበረው የሥራ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ ልጆችን የመደገፍ ስራውን በአንድ ጊዜ ማከናወን ባለመቻላቸው በ55 ዓመት ዕድሜያቸው በገዛ ፍቃዳቸው ጡረታ በመውጣት ሙሉ ጊዜያቸውን በመጠቀም ህልማቸውን እውን ለማድረግ የድጋፍ ስራውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህም እንዲማሩ ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ልጆች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማጥኛ የሚያገለግል ቤተ መጻሕፍት ለመገንባት ከአምቦ ዩኒቨርስቲ የገንዘብ፣ ከዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ የቆርቆሮ እና ከሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ደግሞ የሲሚንቶ ድጋፍ በማሰባሰብ እና ያላቸውን ገንዘብ በመጨመር 110 ካሬ ሜትር በሆነ መሬት ላይ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት አስገንብተው ለአገልግሎት እንዲውልና ልጆቹም ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ የሞሃ ለስላሳ መጠጦች አምራች ፋብሪካ ደግሞ ለተሠራው ቤተ መጻሕፍት የመጽሐፍ መደርደሪያን ጨምሮ፤ የተለያዩ አይነት የትምህርት ቁሳቁሶችን ለአንድ ዓመት የሚሆን ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ የኦሮሚያ ልማት ማህበርም 5 ኮምፒዩተሮችንና 420 መጽሐፍትን ለመጻሕፍት ቤቱ በስጦታ አበርክቶላቸዋል፡፡
ወይዘሮ የሺመቤት በወቅቱ “ልጆች በኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት ሳይማሩ መቅረት የለባቸውም” በሚል መነሻነት በጀመሩት የበጎ ፍቃድ ሥራ፤ የትምህርት ዕድል ያላገኙትን እንዲያገኙ አድርገዋል፤ አሁንም እየሰሩ ይገኛሉ። ይህንን አይነት አስተሳሰብ ሊያዳብሩ የቻሉትም ከውስጥ የመነጨ ፍላጎትና ከቤተሰባቸው የወረሱት የሰጪነት በጎ ምግባር ተዳምሮ እንደሆነ ይገልጻሉ። ቤተሰቦቻቸው ማንም የተቸገረ ሰው እቤታቸው መጥቶ ባዶ እጁን አይመለስም ነበር፡፡ ወደቤታቸው የመጣ ሁሉ በልቶ ጠጥቶ እንዲሄድ ከመደረጉም ባለፈ ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላም ለረጅም ጊዜ የሚጠቀሙበትን እንደ እህል እና እንሰት ተቋጥሮ ሲሰጥ እያዩ ማደጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡
የበጎ ተግባር ተምሳሌቷ እናት ድጋፍ የሚያደርጉት በየትምህርት ቤታቸው ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለሚማሩ ልጆች ሲሆን፤ እስካሁንም 130 የሚሆኑ ልጆችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የተወሰኑት በተለያዩ ሙያ ተሰማርተው ራሳቸውን እየረዱ ይገኛሉ። ዩኒቨርሲቲ ገብተው የተመረቁም አሉ። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችም በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ልጆችን ከማስተማር በተጓዳኝ ተደራራቢ ችግር ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞችንና ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህ አንጻር አምስት አካል ጉዳተኛ ልጆችን በልዩ ሁኔታ በራሳቸው ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በፌስ ቡክና በዩቲዩብ እንዲታወቁና እንዲረዱ አድርገዋል፡፡ በዚህም ለ14 ዓመታት ልጇን አዝላ የነበረች እናት የልጇ መንቀሳቀሻ ዊልቸር እንዳገኘችና ለእሷም የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላት በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው 12 ሴቶችን በልብስ ስፌት አሰልጥነው በማስመረቅ፣ የመስፊያ ማሽንና አስፈላጊ የመስሪያ ቁሳቁሶችን በማሟላት የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡ እንዲሁም ለ9 ሴቶች የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ በመግዛት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በውስጣቸው ሲብላላ የነበረውን ሀሳብ ያካተተ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ያካተተ መጽሐፍ ለምሳሌ ከ600 በላይ ተረትና ምሳሌ፣ ግጥሞች፣ የኦሮሞ ባህላዊ መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ስለሆነው እንሰት እንዲሁም ስለራሳቸው ህይወት ማለትም ስላጋጠማቸው ውጣ ውረድ ጽፈው ከአሳተሙት የመጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ዳቦ ቤት አስገንብተው ለአገልግሎት እንዲውል አድርገዋል፡፡ ከመጽሐፍ ሽያጭ የተረፈውን ገንዘብ ለህጻናት መዋያ ቤት ግንባታ ለማከናወንም መሰረቱ ወጥቷል፡፡ ውስጣቸው የተቸገረን ሰው አይቶ እንደማያልፍ የሚገልጹት ወይዘሮዋ ይህንን በማድረጋቸው የህሊና እረፍት እንደሚሰጣቸውና ደስታቸው እጥፍ ድርብርብ እንደሆነ ነው የሚገልጹት። ይህንን ውስጣዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካትም ነበር የጡረታ ጊዜያቸው ሳይደርስ ቀድመው እስከመውጣት የደረሱት፡፡
በሥራ ሂደት ውስጥ ካጋጠማቸው በርካታ ችግሮች መካከል፡- ድጋፍ ጠይቀው ቀና ምላሽ አለማግኘታቸው በግንባር ቀደምትነት የፈተናቸው መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ የሺመቤት፤ በተለይም ቋሚ ገቢ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ድጋፍ ያለማግኘት ችግራቸውን ለመቅረፍ የሚኖሩበትን ቤት በማከራየት የኪራዩን ገንዘብ የድጋፍ ስራቸው እንዳይቋረጥ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ዋጋ ከፍለውም ቢሆን ልጆቹን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ መቼም ክንዳቸውን እንደማይንተራሱ ይናገራሉ፡፡ “እባካችሁን ባለሀብቶች፣ ተቋማት ችግረኛን እንርዳ” ሲሉም ሰውን ለመስራት ሰው መሆን ነው እና ካላችሁ ላይ ቆንጥራችሁ እገዛ አድርጉ ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
ወይዘሮዋ፤ አስተምረው ለቁም ነገር ካበቋቸው ልጆች መካከል ወጣት ጽኑ ግርማ አንዷ ናት፡፡ ከድርጅቱ ድጋፍ በማግኘት መማር የጀመረችው ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በወቅቱ የ1ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ ነገር ግን በጎ ፍቃድ ድርጅቱ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ስትማር የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ፣ የትምህርት ቁሳቁስ፣ ጫማ፣ ተቀያሪ ልብስ እና እያደገች ስትመጣ የንጽና መጠበቂያ (ሳሙና ሞዴስ) እንዲሁም ዱቄት፣ ጤፍ፣ ብርድ ልብስ፣ ዘይት የመሳሰሉ ቁሳቁሶች ተሟልተውላት መማሯን ትገልጻለች፡፡ ከአስረኛ ክፍል በኋላም በወይዘሮ የሺመቤት ድጋፍ በዲፕሎማ የአካውንቲንግ ትምህርት ተከታትላ ከተመረቀች በኋላ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በዛው ድርጅት ውስጥ የስራ እድል ተፈጥሮላት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጻልናለች፡፡
ወላጅ እናቷ የቀን ሥራ ትሰራ እንደነበር የምትናገረው ወጣቷ፤ ከጊዜ በኋላ ግን እናቷ አቅም በማጣቷ ይህንን ማድረግ አለመቻሏን ታስታውሳለች፡፡ ወይዘሮ የሺመቤት ባይረዷት አሁን የደረሰችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደማትችልም ነው የገለጸችው፡፡ “ብዙ ችግረኛ ልጆች አስተምረው ለቁም ነገር ያደረሱ እና የደሀ እናት የሆኑት እኚህ ልበ ቀና ሴት ረጅም እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው የሁልጊዜ ጸሎቴ ነው” ስትል ነው የበጎነት ተግባራቸው እያስገኘ ያለውን ፍሬ የገለጸችው፡፡
በተመሳሳይ፤ ተማሪ አቤል ግርማ በእሳቸው ድጋፍ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው፡፡ ተማሪው በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ወይዘሮ የሺመቤት ከትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ጀምሮ ሁሉንም አይነት የትምህርት ቁሳቁስ እና ለምግብነት የሚውሉ እንደ ዘይትና ፍርኖ ዱቄት ድጋፍ አድርገው ለዚህ ያበቁት ገና አንደኛ ክፍል ሲገባ ጀምሮ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ ከቁሳቁስ ድጋፉም በላይ በትምህርቱ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ምቹ የማጥኛ ስፍራ ያዘጋጁለት እንደነበረና አልፎ ተርፎም ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ድጋፍ እንዳደረጉለት ይገልፃል። አሁንም በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ውጤታማ እንዲሆን ክትትሉንና ድጋፉን አጠናክረው መቀጠላቸውን ይናገራል። “እሳቸው ከልጅነቴ ጀምሮ ድጋፍ ባያደርጉልኝ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልሜ ዕውን ሊሆን አይችልም ነበር” በማለትም ነው የገለጻቸው፡፡ ተመሳሳይ ግለሰቦች የወይዘሮ የሺመቤትን አርአያነት ተከትለው በችግር ምክንያት የመማር እድል ያላገኙ ወገኖችን ቢታደጉ መልካም ነው ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
በለይላ መሀመድ