
AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም
የሌማት ትሩፋት በስፋት ተግባራዊ በማድረግና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የለሚኩራ ክፍለ ከተማ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች ዶሮዎች ፣ የዶሮ መኖና የዶሮ እርባታ ቤት ሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሎኮ ዳለቻ ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሌማት ትሩፋት በስፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሌማት ትሩፋት የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ገበያን ለማረጋጋት ትልቅ ድርሻ ስላው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
አቅም የሌላቸው እናቶች በሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን እናቶችም የወሰዱትን ግብዓት በአግባቡ መስራት እንዳለባቸው ም/ ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል፡፡
በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ባለፉት 3 ወራት ከ3 ሺ በላይ ለሚሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉ ያነሱት የክፍለ ከተማው የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጸ/ቤት ሀላፊ አቶ አበበ ጌቱ ናቸው ፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው እናቶችም የተደረገላቸው ድጋፍ ራስን በመቻል የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብቻ በቀን ከ300 ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፅዮን ማሞ