ህብረተሰቡ መረጃዎችን በትክክለኛነትና እውነተኛነት ከመቀበሉ በፊት በአግባቡ መመርመር አለበት-አቶ ዛዲግ አብርሃ

You are currently viewing ህብረተሰቡ መረጃዎችን በትክክለኛነትና እውነተኛነት ከመቀበሉ በፊት በአግባቡ መመርመር አለበት-አቶ ዛዲግ አብርሃ

AMN – መጋቢት 20/2017

ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች አማራጮች የሚሰራጩ መረጃዎችን በትክክለኛነትና እውነተኛነት ከመቀበሉ በፊት በአግባቡ መመርመር እንዳለበት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ።

የአፍሪከ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በኢቢኤስ ቴሌቭዠን በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ የተሰራውን የተቀነባበረ የሀሰት ዘገባ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ያለንበት ወቅት እውነት የተፈተነበት ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፥ ውሸት ሀገርን እና ትልልቅ ስልጣኔዎችን እንደሚያፈርስ ጠቁመዋል።

በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ በእውነት ላይ ትልቅ አደጋ መደቀኑን ተናግረዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ “በሁለት ጎን የተሳለ ቢላ ነው” ያሉት አቶ ዛዲግ፥ ስለሆነም ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡና በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአግባቡ ካልተያዘም የህልውና አደጋን የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመው፥ ከሰሞኑ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በተደራጀ መልኩ የተሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ በአብነት ጠቅሰዋል።

ድርጊቱ የብዙ ነገር ምልክት እና በርካታ ፍላጎት ያላቸው አካላት የመሩት መሆኑን በማንሳት፤ጉዳዩ መንግስት ሴቶችን ለማብቃት እያከናወነ ያለውን ስራ ወደኋላ የሚመልስ ነው ብለዋል።

ከዚህም በላይ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ማህበረሰቡን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ለማስገባት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አጀንዳውን ያዘጋጁና ያሰራጩ አካላትም ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ የሴቶችን ክብር የሚነካ እኩይ ተግባር መፈጸማቸውን ነው ያስረዱት።

ድርጊቱ በእውነት ላይ የተቃጣ አደጋ መሆኑን ገልጸው፤ሁሉም ከዚህ ድርጊት ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

ሀሰተኛ መረጃ ማህበራዊ ቀውስን የሚያስከትል መሆኑን አንስተው፥ ህብረተሰቡ የሚጠቀማቸውን መረጃዎች እውነተኛነት በአግባቡ መመርመር እንዳለበት ገልጸዋል።

የመረጃዎችን እውነትና ትክክለኛነት በማረጋገጥ ሂደት ማንም የዳር ተመልካች መሆን እንደሌለበት ጠቅሰው፤ በተለይም ምሁራን በዚህ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review