ህብረተሰቡ ስለ አዕምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ ሊዳብር ይገባል ሲሉ የጤና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
በዋነኛነትም ሴቶች፣ ወጣቶች እና ታዳጊ ወጣቶች ለአዕምሮ ህመም እንደሚጋለጡ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች እና ህፃናት አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ሲስተር ተወዳጅ መርሻ ተናግረዋል፡፡
የዚህም ምክንያት ወጣቶች ዕድሜያቸው ከሚጠይቃቸው እና ማድረግ ከሚፈልጉት ነገር የተነሳ በሰብስታንስ (በአደንዛዥ ዕፅ)፣ በተለያዩ ሱሶች እንዲሁም ከስነተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በወጣቶች ላይ የአዕምሮ ህመም በከፍተኛ ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
በሴቶች ላይም የኑሮ ጫና እና በተፈጥሮ ችግርን ከመቋቋም ከመሳሰሉት ችግሮች አንፃር የአዕምሮ ህመም ከወንዶች በበለጠ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የአዕምሮ ህመም ከትንሹ የስነልቦና ችግሮች አንስቶ እስከ ትልቁ የሥነ አዕምሮ ችግር ድረስ ቁጥሩ ከፍ እያለ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ተጠሪ ሲስተር ፈትለወርቅ ሃይሌ፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተከትሎ የሚከሰት መፈናቀልም ወጣቶችን ለአዕምሮ ጤና ችግር እንደሚያጋልጥ ይገልፃሉ፡፡
ዶክተር ሚካኤል አርጋው በበኩላቸው፣ ወጣቶች ከደባል ሱስ ጋር በተያያዘ ለአዕምሮ ጤና ችግር እንደሚጋለጡ አንስተዋል፡፡
አሁን ባለንበት ጊዜ ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች እና ወጣቶች ለሱስ ያላቸው ተጋላጭነት ከትናንት ዛሬ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
ለዚህም ሱስ አምጪ የሆኑ ነገሮች በየቦታው መገኘታቸው እና አዋዋል የመሳሰሉት ተጠቃሽ ምክንያቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የቅርብ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ደግሞ፣ (FOMO) የተሰኘ የራስን ህይወት ከሌሎች ጋር እያነፃጸሩ ወደ ኋላ ቀርቻለሁ ብሎ የማሰብ እና ለህይወት ትርጉም የማጣት ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች እነዚህን ችግሮች በመገንዘብ ስለ አዕምሮ ጤና ያላቸውን ግንዛቤ ሊያሰፉ እና በባለሙያ የመታየት ልምዳቸውንም ሊያዳብሩ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው