AMN- ኅዳር 11/2017 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ “ህፃናት የሚሉት አላቸው እናድምጣቸው!” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የዛሬ ታዳጊዎች፣ የነገ ሀገር ተረካቢ፣ የወደፊት ተስፋና አለኝታ በመሆናቸው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው በተከበረበትና ማህበራዊ ደህንነታቸው በተረጋገጠበት አገራዊ ድባብ ውስጥ ማደግ ይገባቸዋል ብለዋል።
ህፃናት ፍቅርና ክብካቤ ሳይለያቸው፣ በጎነትን ተላብሰው፣ በእውቀትና በመልካም ስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ማስቻል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።
ህፃናት በራሳቸውም ሆነ በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ ድምፃቸው ጎልቶ እንዲደመጥ፣ በመምከር ሂደትም እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ማበረታታትና ዕድል መስጠት ይገባልም ብለዋል።
ህፃናትን በተመለከተ የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች ለህጻናት መብት፣ ጥቅምና ደህንነት ትኩረትና ቅድሚያ የሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅና ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በተለያዩ አማራጮች መደገፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በዕለቱ በዓሉን ምክኝያት በማድረግ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች፣ የህፃናት ፖርላማ ተወካዮች እና በህፃናት ዙሪያ ለሰሩ ተቋማት እውቅናና ሽልማት መበርከቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።