ህፃናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ሊሠጣቸው ይገባል፡- ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን

You are currently viewing ህፃናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ሊሠጣቸው ይገባል፡- ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን

AMN- ህዳር 11/2017 ዓ.ም

ህፃናት በእውቀትና በመልካም ስነምግባር ታንጸው፣ የተሟላ ጤናና ሰብዕና ኖሯቸው እንዲያድጉ ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ሊሠጣቸው እንደሚገባ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ተናግረዋል

ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ “ህፃናት የሚሉት አላቸው እናድምጣቸው!” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ህፃናት በእውቀትና በመልካም ስነምግባር ታንጸው፣ የተሟላ ጤናና ሰብዕና ኖሯቸው እንዲያድጉና የወደፊት ተስፋቸውም እንዲቃና ከቤተሰብ ጀምሮ ማህበረሰባዊና ተቋማዊ ፍቅር፣ ልዩ ጥበቃ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ ሊሠጣቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደገለፁት፥ ህጻናት በአለምና አህጉር አቀፍ ደረጃ የተጎናጸፏቸውን መብቶች ከሚጥሱ፤ በጤና፣ በአካል፣ በስነልቦናና በማህበራዊ ረገድም ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሚያደርሱ ብሎም ደህንነታቸውን ስጋት ላይ ከሚጥሉና መፃዒ ተስፋቸውን ከሚያጨልሙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች እንዲጠበቁ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ብለዋል።

ህጻናትን አስመልክቶ ሀገራችን ተቀብላ ተግባራዊ እያደረገቻቸው ካሉ አለም አቀፍ ቁልፍ የቃል ኪዳን ሰነዶች መካከል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብቶች ኮንቬንሽነም ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በአለም አቀፍ የሕጻናት መብቶች ኮንቬሽን አንቀፅ 12 የተደነገገውን የህፃናት የተሳትፎ መብት መሠረት በማድረግ በየአመቱ እየተከበረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ለህፃናት ምቹ አገር በመገንባት ረገድ የባለድርሻ አካላትን አጋርነት ለማጠናከርና ምላሽ ሰጪነት ሚና ለማጎልበት በዓሉ ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘንድሮ በዓሉን በማስመልከት በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የህፃናት መብት መከበር፣ የህፃናት ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ህዝባዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል እንዲሁም በተለያዩ አካላትና አካባቢዎች በየደረጃው ሰፋፊ የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎች ሲካሂድ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የህፃናትን ድምፅ በአግባቡ አድምጦ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ብዙዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በየአቅጣጫው የተጀመረው ሀገራዊ የንቅናቄ ስራ ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመድረኩ መገለፁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review