ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ ዕድሮች ገለፁ

እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች በምክክር ለመፍታት የሚጠበቅብንን ሁሉ እንወጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ዕድሮች አስታወቁ፡፡

ዕድሮች ማህበረሰቡ የጋራ ችግሩን በመረዳዳት የሚፈታባቸው ዕድሜና ወዝ፣ ለዛና ደርዝ ያላቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ‘የአንዱ ችግር የሁላችንም ነው፤ በተናጠል የማንፈታውን ችግር በጋራ እናሸንፈዋለን። በብቸኝነት ያጣነውን ደስታ በአብሮነት እናመጣዋለን’ ሲሉ ያቋቋሙት ዘመን የተሻገረ አደረጃጀት ነው፡፡ እነዚህ ማህበራት ከቀብር ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም በመፍታት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም ሀገር በተጣራች ጊዜ ማህበረሰቡን በየአካባቢያቸው በማሰባሰብ ለሀገር ጥሪ ምላሻ በመስጠትም ይታወቃሉ። ዛሬም ሀገር ያሉባትን ችግሮች በምክክር ለመፍታት በተነሳችበት ወቅት ከፊት ከተሰለፉ ማህበራዊ አደረጃጀቶች መካከል ዕድሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሻምበል ብርሃነ ወልደሰንበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የአዲስ ሕይወት የጋራ መረዳጃ ዕድር አመራር

ሻምበል ብርሃነ ወልደሰንበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የአዲስ ሕይወት የጋራ መረዳጃ ዕድር አመራር ናቸው፡፡ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዕድሮችን በመወከል በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው በመጀመሪያው የምክክር ምዕራፍ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ዕድሮች በሀዘንም ሆነ በደስታ ለማህበረሰቡ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸውና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያለምንም ልዩነት አቅፈው የያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ አደረጃጀቶች ህብረተሰቡ በራሳቸው የመሰረታቸው እና ማህበረሰቡ እራሱን በራሱ የሚረዳባቸው፣ የሞተውን በመቅበር፣ ያዘነውን በማፅናናት እና የታመመውን በማስታመም የሚሰሩ በመሆናቸው በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፋችን ለውጤታማነቱ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

እንደ ዕድሮች ለሀገራችን ህመም መድሐኒት በመፈለግ ብሎም ፍቅርን ለማዋለድ እንሰራለን ያሉት ሻምበል ብርሃነ፣ ትውልዱ የተረጋጋ ሕይወትን እንዲመራ ሀገራችንም በምክክር ችግሮቿን እንድትፈታ ህብረተሰቡን በሚገባ በማስገንዘብ እንሰራለን ሲሉም አክለዋል፡፡

አብዱልፈታህ ሁሴን ሲራጅ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የመሊቅ መረዳጃ ዕድር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በክፍለ ከተማ ካሉ ከአምስት መቶ በላይ ዕድሮች  ተመርጠው ክፍለ ከተማቸውን በመወከል በምክክር ምዕራፉ ተካፍለዋል፡፡ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ ዕድር የማያካትተው ዜጋ ስለሌለ ዕድሮች ሀገር ማለት ናቸው፡፡ በመሆኑም የማህበረሰቡ በርካታ ጉዳዮች በዕድሮች የሚነሱ ናቸው፡፡ ይህም በሀገራዊ ምክክሩ ለሚደረገው ተሳትፎ አጋዥ ይሆናል፡፡ ሁሉም ሀሳብ በዕድሮች በመኖሩ ይህ ሀሳብ ተይዞ በምክክሩ ተሳትፎ ተደርጓል፡፡ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ዕድሮች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡

አብዱልፈታህ ሁሴን ሲራጅ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የመሊቅ መረዳጃ ዕድር ሰብሳቢ

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ለአባላቶቻችን አስፈላጊውን ግንዛቤ በመፍጠር የተረጋጋች እና ዘላቂ ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር እንድትኖረን የበኩላችንን እንሰራለን፡፡ ሁሉም ተከባብሮ የሚኖርባት ሀገር ለመገንባትም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለንም፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ የታጠቅ ለድል የመረዳጃ ዕድር ሊቀመንበር አቶ አበራ ኩማ በበኩላቸው፣ “ዕድሮች ትልቅ ማህበራዊ መሰረት ያለን በመሆኑ በሀገራዊ ምክክሩ መወከላችን ለምክክሩ ስኬታማነት ትልቅ አበርክቶ አለው” ብለዋል፡፡ ዕድሮች የማህበረሰብን ችግር ለመፍታት የተቋቋሙ በመሆናቸው ሀገራዊ ምክክሩም ችግራችንን በውይይት የምንፈታበት በመሆኑ አባላቶቻችን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ በተለያዩ የግንኙነት መድረኮቻችን ግንዛቤዎችን በመፍጠርና በምክክሩም በንቃት በመሳተፍ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉም አክለዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review