ለሌሎች የተረፉ የትጋት እጆች

You are currently viewing ለሌሎች የተረፉ የትጋት እጆች

ወይዘሮ ገላኔ ተሊላ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዓለም ባንክ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት በግብርና ስራ በሚያገኙት ምርት ልጆቻቸውን አንደላቅቀው የሚያኖሩ፤ ኑሮ የሞላላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በየዓመቱ ያፍሱበት የነበረው የእርሻ መሬታቸው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ በቀድሞው የአስተዳደር ስርዓት በመወሰዱ ድህነት በድንገት ጓዙን ጠቅልሎ ከተፍ ይልባቸዋል፡፡ ከዚሁ መነሻነት የ11 ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ገላኔ ከነቤተሰባቸው የህይወትን መራራ ገፈት መቅመስ ጀመሩ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮም ለዓመታት ዘለቁ፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደሮች በነባር መሬታቸው ላይ እንዲጠቀሙ በመፈቀዱ የወይዘሮ ገላኔ ቤተሰብ ህይወት ዳግም ይቃና ጀመር፤ በቀድሞ የእርሻ ቦታቸው ላይ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራ በመከወን እጅ እግራቸውን ተብትቦ ከያዘው እጦት መላቀቅ ጀመሩ፡፡

ወይዘሮ ገላኔ መላውን የቤተሰብ አባል በማሳተፍ የከተማ ግብርናውን ተያያዙት፤ የዶሮና የወተት ላሞች እርባታን ጨምሮ የጎመን፣ የቃሪያ፣ የሰላጣ፣ የቲማቲም፣ የድንች፣ የሽንኩርት፣ የጌሾ፣ የቡና፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የማንጎ፣ የብርትኳን፣ የሙዝና የአቮካዶ ልማቶችን በማከናወን ውጤታማ ሆኑ፡፡ በእነዚህ የፍራፍሬ፣ የአትክልትና የእንስሳት ልማቶችም የቤተሰባቸውን ህይወት ከመራራው የድህነት አረንቋ አላቅቀዋል፡፡

ወይዘሮ ገላኔ አሁናዊ አኗኗራቸውን እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ “ወደ አስራ አምስት አይነት የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን እናመርታለን። የአካባቢው ነዋሪዎችና በአቅራቢያው ያሉ የጉሊት ነጋዴዎች ወደ ማሳችን እየመጡ ትኩስ የግብርና ምርቶችን ይገዛሉ፡፡ ከልጆቼ በተጨማሪ ለ10 ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሬአለሁ፡፡ አሁን የቤት አስቤዛን በበቂ ደረጃ ከማሟላት ያለፈ ጥቅም እያገኘን ነው፡፡ ምርቶቻችንን ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እናገኛለን፤ የተሻለ ኑሮም እንኖራለን፡፡”

የከተማ ግብርና የቤተሰብን የዕለት የምግብ ፍጆታ በመሸፈን የኑሮ ውድነት የሚፈጥረውን ጫና የመቋቋም ዕድል ከመስጠት ባሻገር በማህበረሰቡ ውስጥም መልካም የስራ ባህል በማሳደግ እና የአመጋገብ ስርዓትን በመቀየር ረገድም ትልቅ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ወይዘሮ ገላኔ፣ መንግስታዊ ተቋማት በሚያደርጉላቸው የሙያ፣ የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፎች የተሻለ ጥቅም ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በከተማ ግበርና ከሚለሙ የጓሮ አትክልቶች በተጨማሪ የወተት እና የወተት ተዋፅዖ፣ የስጋ ዶሮ፣ የእንቁላል፣ የማርና የዓሳ ምርታማነት ጨምሯል፡፡ በዘርፉ ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል ስለመፈጠሩም ነው ከተጠቃሚዎች አስተያየት ማረጋገጥ የቻልነው።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ አሕመድ በከተማ ግብርና ስራ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ከማሟላት ባለፈ የጓሮ አትክልትና የእንቁላል ምርት ለአካባቢው ነዋሪዎች በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ነግረውናል፡፡                                                                                                                                               

አቶ መሐመድ በቋሚነት ከሚተዳደሩበት የንግድ ስራ ጎን ለጎን ባላቸው ውስን ቦታ የተለያዩ ቁሳቁስ በመጠቀም የጓሮ አትክልቶችን ያለማሉ። እንደ ከተማ የሌማት ትሩፋት ሲጀመር የወረዳው አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት 5 እንቁላል ጣይ ጫጩቶችንና የዶሮ ቤት (ኬጅ) እንዲሁም የዶሮ መድሐኒት ሰጣቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንዴት በጠባብ ቦታ ዶሮ ማርባት እና የዶሮ ምግብ ማዘጋጀት እንደሚችሉ ሙያዊ ድጋፍ አደረገላቸው። ይህም ውጤታማ የሆነ ስራ ለመስራት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡

የወረዳው አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ያደረገላቸው ድጋፍ መነሻ እርሾ እንደሆነላቸው የሚናገሩት አቶ መሐመድ፣ በግል ጥረታቸው 30 ተጨማሪ ዶሮዎችን በመግዛት በየቀኑ የሚያገኙትን የእንቁላል ምርት አሳድገዋል። የቤት ውስጥ የእንቁላል ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ ለጎረቤቶቻቸው በመሸጥ ተጨማሪ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ፣ የከተማ ግብርናን በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ከቤተሰብ የምግብ ፍጆታ ባለፈ የስራ እድል በመፍጠር ረገድም አይነተኛ ሚና አለው፡፡ እርሳቸው በቤታቸው በሚያከናውኑት የከተማ ግብርና ስራ ባለቤታቸውን ጨምሮ 3 ልጆቻቸው የዶሮ መኖ በማዘጋጀት፣ አትክልቶች በመንከባከብና ከቤት የሚተርፈውን እንቁላልና የጓሮ አትክልት በአቅራቢያቸው ባለ ጉሊት በመሸጥ ያግዟቸዋል፤ እግረ መንገድም የስራ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ባላቸው አነስተኛ ቦታ ላይ የጓሮ አትክልት ልማት ስራ የሚያከናውኑት ወይዘሮ መግቢያነሽ ፍሬው፣ የዶሮ እርባታና የአትክልት ልማት ስራውን ከቤት ውስጥ ስራ ጎን ለጎን በቀላሉ እንደሚያከናውኑ ገልፀው፣ የሚያገኙትንም ምርት ከቤተሰባቸው አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኑሮአቸውን እየደጎሙ መሆኑን ነግረውናል። በቀጣዮቹ ጊዜያት ባላቸው ውስን ቦታ ተጨማሪ የዶሮ ኬጅ በማዘጋጀት የዶሮዎችን ቁጥር ወደ 50 ለማድረስ አቅደው እየሰሩ ነው፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ክብሬ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ስራ እንዲጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀው፣ በእንቅስቃሴውም በርካታ አርሶ አደሮች፣ ማህበራትና መስሪያ ቤቶች በመስኩ መሠማራታቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የሌማት ትሩፋት ተግባራዊ ሲደረግ እንደ ወረዳም በስፋት መስራት መጀመሩን ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፣ የምርት አቅርቦት በማሳደግ እና ገበያን በማረጋጋት ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ፣ ቅድሚያ በወረዳው ሰፊ የግል ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በይዞታቸው ላይ የከተማ ግበርና ስራን እንዲያከናውኑ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ የተሰራ ሲሆን፣ በመቀጠልም ማንኛውም መሬት ፆም እንዳያድር በሚል ሁሉም ማህበረሰብ ባለው ቦታና ባገለገሉ ቁሶች ጭምር የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ለቤት ፍጆታ እንዲጠቀም የማድረግ ስራ ተሰርቷል። ይህም አበረታች ውጤት አስገኝቷል፡፡ በተለይ በበዓላት ወቅት የምርት እጥረት እንዳያጋጥም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በወረዳው ከ4 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ እንደተሳተፉ የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 52ቱ ባላቸው ሰፊ የእርሻ ማሳ የከተማ ግብርናን የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ በይዞታቸው ጥሩ ስራ ሰርተው ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች በመሰራታቸው በርካቶች ዘርፉን መቀላቀላቸውን አስረድተዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትና የአመጋገብ ዘይቤን ለማስተካከል የከተማ ግብርናን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ ስራው በአነስተኛ ግቢና በወዳደቁ እቃዎች እንዲሁም በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በእድር ቤት ግቢዎች እና በጥቅሉ መገኛቸውን በወረዳው ውስጥ ባደረጉ በ25 ተቋማት ጭምር 6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ፉርጋሳ እንደ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለው፣ ከግለሰቦች በተጨማሪ ተቋማትን ወደ ዘርፉ በማስገባት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ክፍለ ከተማው የማስፋፊያ አከባቢ እንደመሆኑ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ስራዎች በሰፊው ይሰራሉ ያሉት ኃላፊዋ፣ የተገኙ የእንሰሳት ተዋፅኦዎችና የግብርና ምርቶችንም በሰንበት ገበያዎች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ከነጋዴዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር አምራችና ሸማች በፍትሐዊ የንግድ ሰንሰለት እንዲገናኙ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ወይዘሮ ሰብለ በገለፃቸው፣ ግንዛቤ በመፈጠሩም በርካቶች ወደ ስራ ገብተው በዘርፉ ሞዴል  አልሚዎች መፈጠራቸውንም ነው ያስረዱት፡፡ እንደ አጠቃላይ በመንግስት እና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በእድሮች ጭምር ባሉ ባዶ ቦታዎች የሌማት ትሩፋት ስራንና የከተማ ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡ በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የጓሮ አትክልትን ጨምሮ 2 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በሰብል ልማት መሸፈኑን ጠቁመዋል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ         

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review