
AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም
በህመም ላይ የነበረች ቡችላዋን በአፏ አንጠልጥላ ወደ ህክምና ተቋም የወሰደችው ውሻ መነጋገሪያ ሆናለች፡፡
ይህ ልብ የሚነካ እውነት የማይመስል ታሪክ የተፈጠረው በቱርክ ኢስታንቡል ነው፡፡
አንድ የተቀረጸ የሲሲቲቪ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው ፣ አንዲት ውሻ አዲስ የተወለደች ቡችላዋን በአፏ አንጠልጥላ የእንስሳት ህክምና ክሊኒክ በር ላይ በጥንቃቄ ስታስቀምጥ ያሳያል፡፡
ከዚህ ከውሻዋ ተግባር ቀደም ብሎ የተፈጠረውን ሁኔታ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሲያስረዱ፣ የእንስሳት ወዳጅ የሆነ አንድ ግለሰብ መንገድ ዳር ወድቃ ያገኛትን አንዲት ቡችላ በማንሳት በቱርክ ኢስታንቡል ግዛት በበይልክዱዙ አድናን ካህቬቺ መንደር ውስጥ ወደሚገኝ ክሊኒክ ህክምና እንድታገኝ ይዞ ይመጣል።
በክሊኒኩ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችም ቡችላዋን ለማከም በሚሯሯጡበት ወቅት ነበር ነገሩን በቅርበት ስትከታተል የነበረችው የቡችላዋ እናት ሌላ ተጨማሪ በህመም የምትሰቃይ ቡችላ በአፏ አንጠልጥላ ወደዚህ የእንስሳት ህክምና ክሊኒክ ይዛ በመምጣት በጥንቃቄ በክሊኒኩ ደጃፍ ላይ ያስቀመጠችው፡፡

በክሊኒኩ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ የተጨነቀችው እናት ውሻ የጤና ባለሙያውን ተከትላ በመግባት ህክምና የሚደረግላቸው ቡችሎቿን በአይኗ ስትከታተል ያሳያል፡፡
ህክምና የተደረገላቸው ቡችሎቹ ‘ሃይፖተርሚያ’ በተባለ የብርድ በሽታ የተጠቁ እና ዝቅተኛ የልብ ምት የነበራቸው እንደነበሩ የህክምና ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡
እንደ እድል ሆኖ፣ ዶክተር ባቱራልፕ ኦጋን እና ቡድናቸው ቡችሎቹን ማዳን የቻሉ ሲሆን አሁን ሶስቱም በክሊኒኩ ውስጥ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
እስካሁን ህክምናው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን እና ሁለቱ ቡችሎች እና እናታቸው ለጥቂት ቀናት በክሊኒኩ ውስጥ እንደሚቆዩም ዶክተር ባቱራልፕ ተናግረዋል፡፡ ለጤንነታቸው ሲባልም ጎብኚዎችን እንደማያስተናግዱ ነው የተናገሩት።
ለቡችሎቿ ያላትን ፍቅር በተግባር ያሳየችው የዚህች ውሻ ታሪክ በርካቶችን አስገርሟል፡፡ እንዴት ያለች አስተዋይ እና አሳቢ ውሻ ነችም አስብሏል፡፡
ተንቀሳቃሽ ምስሉ በኢንተርኔት መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእንስሳት አፍቃሪዎች ለውሾቹ እገዛ እያደረጉ እንደሆነም ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው አስነብቧል፡፡