AMN- ጥር 20/2017 ዓ.ም
አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ድርጅት፣ አገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን በተመለከተ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “በጠረጴዛ” ከተሰኘው የቴሌቪዥን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ተቋሙ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን እና የባቡሮችም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ትኩረት እና ባከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች አገልግሎት አሰጣጡ ባለፉት 7 ወራት ከነበረበት መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ከሰባት ወር በፊት ተቋሙን ሲረከቡ 13 ባቡሮች እንደነበሩ ያነሱት ዶክተር ብርሃን፣ በተደረገ ሰፊ ርብርብ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮችን ቁጥር ወደ 18 ማድረስ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋሙ አሁንም የሚገባውን አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡
ድርጅቱ በመንግስት የሚደገፍ ተቋም መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሁንም በየዓመቱ ከመንግስት 500 ሚሊየን ብር እየተደጎመለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በድርጅቱ ያሉ ችግሮችን እልባት የመስጠት ሃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ እንደሆነ በማንሳትም ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች በማየት ከችግሩ እንዲወጣ አዲስ አመራር በመመደብ በ6 ወራት ውስጥም 5 ባቡሮችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ይህንኑ በማስቀጠል የተቀሩትን ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ባቡሮችን ወደ አገልገሎት ለማስገባት ሰፊ ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
በታምራት ቢሻው