AMN- የካቲት 7 /2017 ዓ. ም.
ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ፡፡
በሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክረው የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቦት ቢን ናህያን አልናህያን፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚሁ ወቅት፤ በሱዳን የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ችግሩን ታሳቢ ያደረገ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለሱዳን ሰብዓዊ ድጋፍና ምላሽ እንዲሁም ከሱዳን ውጪ ለሚገኙ ስደተኞች ምላሽ ለመስጠት የሚሆን እቅድ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
እቅዶቹን ለማስፈጸም ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህም በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሱዳናውያን ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚውል አብራርተዋል።
በሱዳን በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ተፋላሚ ኃይሎች የሰብዓዊ ድጋፍ መርሆችን ሊያከብሩ እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ግጭት እየተካሄደባቸው ባሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው በሱዳን ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው አካታች በሆነ ውይይት ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ህብረትም ችግሩ አፍሪካዊ በሆነ መፍትሄ እንዲፈታ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ እየተሰጠ ያለው ምላሽ በቂ አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት(ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ናቸው።
ከችግሩ ስፋት አኳያ ቀጣይነት ያለው ቅንጅታዊ ምላሽ አሰጣጥ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።