ለብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው

You are currently viewing ለብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርሐ-ግብር እየተካሄደ ነው

AMN – መጋቢት 6/2017 ዓ.ም

በብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ለ2ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የተዘጋጀ የእውቅና መርሐ ግብር በስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋናው ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ ን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሀላፊዎች፣ ባለሀብቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ያካሄደው የፓርቲው 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና 2ኛው ጠቅላላ ጉባኤ፣ ፓርቲው ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅም እሳቤ እንዳለው እና በቀጣይነትም ሀገሪቱን የሚያሻግሩ ውሳኔዎች የተላለፈበት መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋናው ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።

“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መርህ ሀሳብ ሲከናወን የቆየው የፓርቲው 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና ከቃል እስከ ባህል በሚል ሁለተኛ ጉባኤውን ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እንዳሉት፣ ፓርቲው በጉባኤው የህዝቡን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ጉዳዮች፣ ሙስና፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ሰላምን፣ ማህበራዊ ፍትህ እና ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከቱ ጉዳዮች ቀጣይ አቅጣጫ የተቀመጠበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪ የፓርቲው ጥራት እና ጥንካሬ የታየበት እና የኢትዮጵያን መፃኢ እድል ዓለም እንዲገነዘበው እድል የፈጠረ መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ብቃት ያላቸው አመራሮች የተመረጡበት ስለመሆኑም አቶ አደም ገልፀዋል።

በመድረኩ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review