
AMN – ታኀሣሥ 7/2017 ዓ.ም
“ለነገዋ” የሴቶች ተሀድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል እና ብርሃን የአይን ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ለሌሎች ተሞክሮ መሆን የሚችሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መሆናቸውን የፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን አስታወቀ፡፡
በፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ የተመራ የፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተሰሩ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተሰሩ ሰው ተኮር ስራዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያቃልሉ እና ግብርናና ኢንዱስትሪን አጣምረው ውጤታማ የሆነ ስራ መስራት እንደሚቻል ማሳያ መሆናቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ገልጸዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎች የ10 አመቱን የልማት እቅድ ለማሳካት ማሳያ መሆን የሚችል የተቀናጀ ስራ እንደሆነም ዶ/ር ፍጹም ተናግረዋል።
“ለነገዋ” የሴቶች ተሀድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል እና ብርሃን የአይን ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ለሌሎች ተሞክሮ መሆን የሚችሉ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ናቸዉ።
“ለነገዋ” የሴቶች ተሀድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የበርካታ ሴቶችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚቀርፍ ስራ እንደሆነም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ብርሃን የአይን ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ የብልጽግና ሰው ተኮር መርህን ያሳየ እንደሆነም ገልጸዋል።
የፌዴራል የሱፐርቪዥን አባላት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፣ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸግ ማዕከል፣ ብርሃን የአይን ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ፣ በግለሰብ የለማ የከተማ ግብርና ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሰብል እና የጥራጥሬ የገበያ ማዕከል ፣ በወረዳ 03 የሚገኘው በባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ እየተገባ የሚገኘው የአቅመ ደካማ ቤት እና በየካ ክፍለ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የጫካ ፕሮጀክት እና የወንዝ ዳርቻ ስራዎችን እየጎበኙ ነው።
በዳንኤል መላኩ