
AMN – ኅዳር 12/2017 ዓ.ም
ለአምስተኛ ጊዜ የተከበረው የሳይበር ደህንነት ወር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
አስተዳደሩ አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር መጠናቀቁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ፤ በመግለጫቸው የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሳይበር ደህንነት ወር የተቋማትን እና የማህበረሰቡን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚህም የተሳካ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
በጥቅምት ወር በተካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ የአጭር ፊልም ውድድር መካሄዱንም ገልጸዋል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁ እንደየ ደረጃቸው ከ50 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ሽልማት እንደተበረከተላቸው ጠቁመዋል።
አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የተፈለገውን አላማ በማሳካት በኩል ውጤታማ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሳይበር ደህንነት ወር “የቁልፍ መሰረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች መከበሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡