
በየካ ክፍለ ከተማ ብቻ በመንግስት ተቋማት 51 የህፃናት ማቆያዎች ተቋቁመው 930 ህጻናትን ተጠቃሚ አድርገዋል
በከተማዋ አዲስ የስራ ባህልን ለማዳበር የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ጥረቶች ሲደረጉ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በተለይ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ከመደበኛው የስራ ሰዓት ውጭ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዲፈጠሩ ከማድረግ አንፃር ጉልህ መሻሻሎች ይስተዋላሉ። ከእነዚህም የእናቶችን ጫና በማቅለል ሙሉ ትኩረታቸውን በስራ ገበታቸው ላይ እንዲያደርጉ ያስቻለው የህፃናት ማቆያ አገልግሎት ተጠቃሽ ነው።
በመንግስት ተቋማት የተቋቋሙት እነዚህ የህፃናት ማቆያዎች የሴቶችን ጫና በማቃለል ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው እናቶችም ይመስክራሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ተዘዋውረን የህፃናት ማቆያዎቹ ያሉበትን ሁኔታ በቃኘንበት ወቅት ያነጋገርናቸው እናቶች አገልግሎቱ እፎይታ እንዳስገኘላቸው ገልፀዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ንብረት አስተዳደር ፅህፈት ቤት የመረጃ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ኮከብ አዱኛ የተቋሙ የህጻናት ማቆያ ተገልጋይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ማቆያው ልጃቸውን በቅርበት የመከታተልና የመንከባከብ ዕድል ስለፈጠረላቸው በተረጋጋ መንፈስ ስራቸውን እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው ገልፀውልናል፡፡
በተቋማቸው የልጆች ማቆያ መዘጋጀቱ ልጃቸውን በየሁለት ሰዓቱ ጡት እንዲያጠቡና ትኩስ ትኩስ ምግቦችን በመመገብ የልጃቸው ጤና አስተማማኝ እንዲሆን በማድረጉ እጅግ መደሰታቸውንና ስራቸውንም በተረጋጋ መንፈስ በውጤታማነት ለመስራት እንዳለው አስረድተዋል፡፡
የህፃናት ማቆያዎች በየተቋሙ መቋቋማቸው የእናቶችን ጫና በማቃለል በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም ሌላ ህፃናት ነገ የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ፣ ብቁና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ነው የገለፁት፡፡
ሴቶችን ወደኋላ ከሚያስቀሯቸው ምክንያቶች አንዱ ልጆቻቸውን በአግባቡ የሚንከባከብና የሚይዝላቸው ሰው እጦት እንደሆነ የጠቆሙት ወይዘሮ ኮከብ፣ በመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተቋቋሙ የህፃናት ማቆያዎች የእናቶችን ጫና በማቃለል በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በህፃናት ማቆያ በሞግዚትነት የምታገለግለው ወጣት እጥፍወርቅ ሞገስ ህፃናት ልዩ ትኩረት እንደሚሹ አውስታ፣ እርሷም ምን እንደሚፈልጉና እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ጠንቅቃ በማወቅ ኃላፊነቷን እየተወጣች እንደሆነ ተናግራለች፡፡
ህፃናቱን እንደእድሜ ደረጃቸው በተገቢው መንገድ እንደምትንከባከባቸው ገልፃ፣ በተለይ ከ2 እስከ 4 ዓመት ያሉትን ከመንከባከብ ባለፈ በሙዚቃና በጨዋታ መልክ እያዋዛች መሰረታዊ ነገሮችን እንደምታስተምራቸው ነው ያስረዳችው፡፡
የሁለት ዓመት ልጃቸውን በህፃናት ማቆያው አስገብተው ወደ መደበኛ ስራቸው ሲገቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ አበበች ክንዱ የተባሉ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ በተቋማት አካባቢ የሚከፈቱ የልጆች ማቆያዎች ትልቅ እፎይታን የሚሰጡ እንደሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
በስራ ቦታ የህፃናት ማቆያ አለመኖር በተለይ ለእናቶች ተደራራቢ ጫናን የሚፈጥር ነው ብለው፣ ልጆች እቤት ሲውሉና በማቆያዎች ሲውሉ ከባህሪ አኳያም ልዩነት እንዳላቸው ተናግረዋል። በህፃናት ማቆያ ሲውሉ ከሌሎች ልጆች ጋር በቀላሉ መግባባትና በጋራ የመጫወት፣ ለመመገብ ያለማስቸገር ብሎም ነገሮችን በራሳቸው የመሞከር ልማዳቸው የተሻለ ከመሆን ባለፈ ስርዓትም እንደሚማሩ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የቤት ሰራተኛን አምኖ ልጅ ትቶ መውጣት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱም በርካታ እናቶች ልጅ ሲወልዱ ስራቸውን እያቋረጡ ቤታቸው እየዋሉ ነው ብለው፣ ሴቷ በተማረችበት ሙያ ሀገሯን ማገልገልና ኑሮዋን መምራት እየቻለች እቤት መዋል እንደሌለባት፤ የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ለሴቶች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ በመንግስት ተቋማት እየተሰጠ ያለው ይህ የህፃናት ማቆያ አገልግሎት በግል ተቋማትም መተግበር አለበት ብለዋል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አስተዳደር የሴቶች፣ ሕፃናትና ማበራዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት የህፃናት ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ደመቀ ነጋሽ በበኩላቸው በወረዳው በተቋቋመው የህፃናት ማቆያ እድሜያቸው ከ4 ወር እስከ 4 ዓመት ያሉ 20 ህፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመንግስት ተቋማት የቀን የህጻናት ማቆያዎች መመቻቸታቸው ሴቷ ልቧ ሳይሰቀል ስራዋን ተረጋግታ እንድትሰራ፣ ህፃናቱም የእናታቸውን ጡት እንዲጠቡና ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲያድጉ ከማድረጉም ሌላ ሴቶች ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አቶ ዳንኤል አብረሃ በየካ ክፍለ ከተማ ሴቶች ህፃናት ማበራዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የቀዳማይ ልጅነት እድገት ማሰፋፊያ ባለሙያ ናቸው፡፡ በክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ግቢ ያለውን ጨምሮ በ12ቱም ወረዳዎች የህፃናት ማቆያዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የማቆያው ዋንኛ ዓላማ ሰራተኞች ልጆቻቸው ጤናማ በሆነ መልኩ ተጠብቀው እነሱም ስራቸውን በአግባቡ በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ያሉት ማለሙያው፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ በተቋቋመው የህፃናት ማቆያ 30 ህፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውንና የተቋሙ መከፈት የወላጆችን ጫና በማቃለል ስራቸውን በሙሉ ልብና ኃላፊነት እንዲሰሩ አድርጓል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ፣ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ አንፃር የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ ሲሄዱ ልጆቻቸውን የሚንከባከብላቸው ሰራተኛ ቀጥረው ለማሰራት በተለያዩ ምከንያቶች ይቸገራሉ። ልጆቻቸውን በተቋማቸው በተቋቋመው ማቆያ ማዋላቸው ደግሞ ወጪያቸው እንዲቀንስ ብሎም ልጆቻቸውን በቅርበት ለመከታተል ያስችላቸዋል፡፡
የክፍለ ከተማ አስተዳደሩ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማበራዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እናቴነሽ አለማየሁ እንደገለፁት የሴቶችን ማህበራዊ ጫና በመቀነስ በስራቸው ውጤታማና ምርታማ እንዲሆኑ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
ከእነዚህም አንዱ በመንግስት ተቋማት የህፃናት የቀን ማቆያዎች መቋቋማቸው ተጠቃሽ ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ይህም የእናቶችን ጫና በመቀነስ በተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በተጨማሪ የህፃናትን ደህንነት በመጠበቅ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከመፍጠር አኳያም የጎላ ድርሻ እንዳለው ነው ያብራሩት፡፡
እንደኃላፊዋ ማብራሪያ፣ ሴቶች ስራቸውን እየሰሩ ልጅ ወልደው ለማሳደግ በእጅጉ መፈተናቸው አይቀርም፡፡ በተለይ እለት ከእለት እየተባባሰ የመጣው የቤት ውስጥ አጋዥ ደመወዝና ሌሎች ወጭዎች ከመጨመራቸውም ሌላ ልጆቻቸውን እቤት ጥለው ተረጋግተው ስራቸውን ለመስራት ይቸገራሉ፡፡
ህፃናት አእምሯዊና አካላዊ እድገታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ከተፈለገ እድሜያቸው ቢያንስ ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው የእናት ጡት ወተት በሚገባ መጥባት እንዳለባቸው የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም በተቋማት የህፃናት ማቆያዎችን ማስፋፋት ተመራጭ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ከዚህ አኳያ በመንግስት ተቋማት የሚቋቋሙ የህፃናት ማቆያዎች ለሴቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለስራቸው ወጤታማነት ብሎም ጤንነቱ የተጠበቀና የተነቃቃ ትውልድ ለመገንባት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ያወሱት ወይዘሮ እናቴነሽ፣ በክፍለ ከተማው በጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤቶች፣ በአስራ ሁለት የወረዳ አስተዳደሮች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት 51 የህፃናት የቀን ማቆያዎች መቋቋማቸውን እና 930 ህጻናት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደክፍለ ከተማ የህፃናት ማቆያዎች ተደራሽ ሳይሆኑ በፊት በርካታ እናቶች ስራቸውን ተረጋግተው መስራት ስለማይችሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ችግር ከመፍጠሩም ሌላ በዚሁ ችግር ምክንያት ስራቸውን አቋርጠው እቤት ለመዋል የተገደዱ ሴቶች እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡
አሁን ላይ ግን ይህ ችግር በመወገዱ ሴት ሰራተኞች ስራቸውን ተረጋግተው በውጤታማነት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀው፣ በቀጣይም እንደ ክፍለ ከተማ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ጭምር ተግባሩን በማስፋት የሴቶችን ውጤታማነትና የተሻለ ትውልድ የመገንባት ግብ ለማሳካት አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ