ለኮንፍረንሶች ተመራጭ የሆነች ከተማ – አዲስ አበባ

AMN – ታኅሣሥ – 14/2017 ዓ.ም

የተለያዩ አለም ሀገራት አለምአቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገዳቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያገኛሉ።

አለም አቀፍ ኮንፈረንስን ማስተናገድ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው እንዲነቃቃና እድገት እንዲያሳይ ፣ አለምአቀፋዊ መገለጫ የሆኑትን ባህልና እሴቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ፣መሰረተ ልማቶቻቸውን ለማዘመን እና የባህል ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ለማድረግና አቅም ለማጎልበት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ፡፡

በዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተመራጭ የኮንፍረንስ ከተማ መሆን ከተቻለ ደግሞ ይህ ተጠቃሚነት ዘለቄታዊ እንዲሆን ያደርገዋል ፡፡

አዲስ አበባ ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥሎ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደሆነች ለዓመታት ሲነገር የቆየ ሀቅ ነው፡፡

በያዝነው አመት ብቻ መዲናችን አዲስ አበባ ወደ 30 የሚጠጉ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎችን በስኬትና በድምቀት አስተናግዳለች ፡፡

በቅርቡ በአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተካሄዱ ትላልቅ ኮንፍራንሶች ውስጥ 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠቀስ ነው፤ ኮንፍረንሱ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮችን ሰብስቦ በአፍሪካ እግር ኳስ ማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ተወያይቷል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (CAF) 46ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከመጡት እንግዶች መካከል የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔና የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ጆያኒ ቪንቼንዞ ኢንፋንቲኖ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

መዲናችን አዲስ አበባ በቅርቡ ያስተናገደችው ሌላኛው ኮንፈረንስ ደግሞ “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፓን-አፍሪካን አዳራሽ የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ነበር ፡፡

አዲስ አበባ የተማሪዎች እና የአረጋውያን ምገባ ማእከላት የሚገኙበት፣ የቅድመ-ልጅነት እድገት ማዕከላት የተስፋፉባት፣ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከላት የተገነቡባትና ለወጣቶች ሰፋፊ የስራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ለማወቅ መቻላቸውን የኮንፍራንሱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

እንዲሁም አዲስ አበባ በፍጥነት እየተለወጠች የመጣችና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገች የመጣች ከተማ መሆኗን ለመታዘብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው አዲስ አበባ ካስተናገደቻቸው አህጉራዊና አለምአቀፋዊ ስብሰባዎች ውስጥ “ከረሀብ ነጻ ዓለም” (World Without Hunger) የተሰኘው አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ተጠቃሽ ሲሆን ይህ ኮንፈረንስ ረሃብን ለማጥፋት እና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ያለመ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎችና እቅዶች ላይ አተኩሮ የመከረው ጉባኢ አንዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ሽግግር እና ምርታማነት ላይ በማተኮር በተሰራው ሥራ የታረሰ መሬትን በእጥፍ በማሳደግ ከፍ ያለ እሴት ባላቸው የኢንደስትሪ አዝርዕት ምርቶች ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

ረሃብን መዋጋት የጋራ ምላሽን ይሻል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ለምግብ ዋስትና የሚሆን የአለምአቀፍ ድጋፍ አቅርቦት፣ ድንበር ዘለል የሆነ እውቀትና ልምምድ፣ ለፍትሃዊ ተደራሽነት የሚረዳ የፖሊሲ መናበብ ብሎም ለሴቶች ትኩረት የሚሰጥ የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች ድጋፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በሌላም በኩል “የበለጸገና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ የአፍሪካ የሰላም ኮንፈረንስ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ስብሰባው ሰላም የሰፈነባት፣ የበለጸገችና የለማች አፍሪካን እውን ለማድረግ ውይይት የተደረገበት መድረክ ነበር ።

ሌላኛው አዲስ አበባ ያስተናገደችው አለምአቀፍ ጉባኤ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች ኮንፈረንስ ሲሆን ስብሰባው በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ውይይትና መግባባትን በመፍጠር፣ ሰላምና ትብብርን ማስፈን ነበር።

ኮንፈረንሱም ከተለያዩ ቤተ እምነት የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶች ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተሳተፉበት ነበር፡፡

ከነዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዙሪያ የመከረዉ የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ፣ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበር ጉባኤ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት (UNIDO) ጉባኤ፣ የዩኔስኮ (UNESCO) በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መከላከል ቀን መታሰቢያን ምክንያት የተደረገ ውይይት እና ሌሎችም በርካታ መድረኮች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፡፡

ከነዚህ ሁነቶች ማየት እንደሚቻለውም አሁን አሁን አዲስ አበባ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በአዲስ አበባ በብዛት እየተካሄዱባት ይሄ ማለት ደግሞ ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹና ተመራጭ እየሆነች መጥታለች ማለት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም እየጎለበተ መምጣትና ከተማዋ በሁለንተናዊ ፈጣን ለውጥ ውስጥ መገኘት ለመድረኮቹ መምጣት ሚናቸዉ የላቀ እንደሆነ ተገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ ተሰሚነት እያደገ መምጣት፣ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ዘርፍ እየታየ ያለዉ መሻሻል መዲናዋ የበርካቶችን ቀልብ እንድትስብና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከል እንድትሆን እያስቻላት መጥቷል፡፡

በፍጥነት እየተለወጠ ከመጣው የመሰረተ ልማት እድገትና በዲፕሎማሲ ረገድ ከተመዘገቡ ድሎች በተጨማሪ ምቹና ለጤና ተስማሚ የአየር ሁኔታ መኖር፣ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና እየዘመነ የመጣና ባህላዊ እሴቶችን ያካተተ መስተንግዶ፣ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም መኖር አዲስ አበባ ኮንፍረንሶችን በስኬት እንድታስተናግድ ከማስቻሉም ባለፈ መዲናዋን ከቀድሞው በላቀ መልኩ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ይገኛሉ ።

በሽመልስ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review