AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው እየተባባሰ ለመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ልዩ ልዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶች እንደ ምክንያትነት የሚገለጹ ቢሆንም ለእይታ ግልፅ ያልሆኑ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች መበራከት ለአደጋ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶች ከአንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሦስት ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች በትራፊክ ፖሊስ አባላት ብቻ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በጥር ወር 2017 ዓ/ም ብቻ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ከ2 ሺ 1 መቶ በላይ አሽከርካሪዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው የተባለው፡፡
ፖሊስ በየጊዜው የታጠፈ የደበዘዘ እና የተፋፋቀ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ያስታወቀው ፖሊስ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓትን በመፍጠር ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው ደምብ ቁጥር 557/2016 መሰረት ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 1ሺ 5 መቶ ብር የሚያስቀጣ ደምብ መተላለፍ መሆኑን ተደንግጓል፡፡
በአዲስ አበባ የአደጋም ሆነ የወንጀል ስጋቶችን መቀነስ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በመደበኛነት ከሚያከናውነው የትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ጎን ለጎን ከየካቲት16 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በዘርፉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የታጠፈ፣ የተቆረጠ፣ የደበዘዘ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ችግሩን በማረም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።