ለጠላት የማይበገር ክንደ ብርቱ የመከላከያ ሰራዊት ተገንብቷል – ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

AMN-ግንቦት 03/2017 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት ለጠላት የማይበገር ክንደ ብርቱ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።

የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በነቀምቴ ስታዲየም እየተከበረ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሰረት፣ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖችና ሌሎች አመራር አባላት ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እና የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ታድመዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ እና የማጽናት ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዳይረጋገጥ ለማድረግ የሚጥሩ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ሰላም እያሰፈነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ክንደ ብርቱ ሰራዊቱ መስዋዕትነት በመክፈል የጠላትን ሴራን በማክሸፍ ኢትዮጵያን እያጸና እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የምዕራብ ዕዝ መንግስት እና መከላከያ ሰራዊት የሚኮሩበት ጀግና ዕዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዕዙ የኢትዮጵያ ጋሻ በመሆን ሀገሩን እየጠበቀ ይገኛል ብለዋል።

ዕዙ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚቃጡ ማንኛውንም ጥቃት በመመከት ሀገርን እያኮራ ይገኛል ሲሉም ገልፀዋል።

ሰራዊቱ በአሸባሪው ሸኔ እና በጽንፈኛው ላይ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን እያረጋገጠ እንደሚገኝም ጨምረው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ አሁንም ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ምዕራብ ዕዝ በየትኛውም ቦታ በመንግሥት የተሰጡትን ግዳጆች በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሠለ መሰረት ናቸው።

ዕዙ በጽናት ሀገሩን እየጠበቀና የተሰጡትን ግዳጆች በጀግንነት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸው፤ የሀገሪቱን ዳር ድንበር በመጠበቅና ሰላም በማረጋገጥ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጋሻ የሆነው ምዕራብ ዕዝ በየትኛውም ቦታ ህዝባዊ ባህሪን በመላበስ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም የታላቁ የህዳሴ ግድብን በመጠበቅ እና ለግድቡም ቦንድ በመግዛት ህዝባዊነቱን ያረጋገጠ ዕዝ ነው ብለዋል።

የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review