ሊውስ ሱአሬዝ ያቋቋመውን ቡድን እንዲቀላቀል ሊዮኔል ሜሲን ጋበዘ

You are currently viewing ሊውስ ሱአሬዝ ያቋቋመውን ቡድን እንዲቀላቀል ሊዮኔል ሜሲን ጋበዘ

AMN-ግንቦት 20/2017 ዓ.ም

ሊውስ ስዋሬዝ 2018 ላይ ለታዳጊዎች እድል መስጠት የሚችል ቡድን ለማቋቋም ይነሳል፡፡በቤተሰቡ ድጋፍ ሃሳቡን 2021 ላይ እውን ለማድረግ ይንቀሳቀሳል፡፡ ቡድኑንም ዲፖርቲቮ ኤል ኤስ ኤም የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡

መቀመጫውን ሲኡዳድ ዴ ላ ኮስታ ያደረገው ቡድኑ እስካሁን ከ3 ሺ በላይ አባላትን ማፍራት ችሏል፡፡ 80 ሺ ስክዌር ሜትር ቦታ አግኝተው 1ሺ400 ተመልካች የሚይዝ ሜዳ ሰርተዋል፡፡

ሊውስ ስዋሬዝ ቡድኑን ይበልጥ ለማጠናከር ለበርካታ ዓመታት አብሮት የተጫወተውን እና የቅርብ ጓደኛውን ሊዮኔል ሜሲን ጋብዞታል፡፡

እንደ ኢ ኤስ ፒ ኤን ዘገባ የሊዮ ሜሲ ድርሻ ባይታወቅም ሃሳቡን ተቀብሎ ለማገዝ ግን ዝግጁ ነው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ከሊውስ ስዋሬዝ ጋር በጋራ በመሆን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ ’’እኔን ስለመረጥከኝ ክብር ተሰምቶኛል ፤ ለቡድኑ የምችለውን ለማገዝ ዝግጁ ነኝ ፤ ከምንም በላይ ከአንተ ጎን በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ፡፡’’ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ዲፖርቲቮ ኤል ኤስ ኤም በቡድኑ ስም ኢንስታግራም ገፅ እውን ባደረገ ሁለት ሰዓታት ውስጥ 40ሺ ተከታዮችን አፍርቷል፡፡

ቡድኑ በ2026 በኡራጓይ አራተኛ የሊግ እርከን ላይ የመወዳደር ፍቃድ አግኝቷል፡፡ የቀድሞ የኡራጓይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አልቫሮ ሪኮባ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይመራል ተብሏል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review