ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሰላም ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? እጅግ በጣም ጥሩ ነው እንደምትሉ እርግጠኞች ነን፡፡ ልጆች ከትምህርታችሁ በተጓዳኝ የተለያየ ተሰጥኦ አላችሁ አይደል? ልጆች ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ የተለያዩ የፈጠራ ስራ የሰራውን የተማሪ ዮርዳኖስ አቡን ነው፡፡ ተማሪ ዮርዳኖስ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በቡርቃ ቦሪ አንደኛና መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡
ልጆች ተማሪው ከሰራቸው የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች መካከል አንዱ ቤት የሚጠብቅ መሳሪያ ነው፡፡ በተለይም አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን ከአደጋ እንዲከላከሉ የሚያስችል መሳሪያ ነው። ፈጠራው በቤቱ በር ወይንም አጥር ላይ ነው የሚገጠመው፡፡ የተማሪው ፈጠራ በመኖሪያ ቤትም ሆነ በንግድ ተቋም ዘራፊ ቢመጣ ገና የቤቱን በር ወይንም ገና የውጪውን አጥር ሲነካ መሳሪያው ሴንሰር የተገጠመለት በመሆኑ ድምፅ ያሰማል፡፡ ድምፁ ግለሰቡ ተኝቶም እንኳን ቢሆን እንዲነቃ ያደርገዋል፡፡ የቤቱ ባለቤት ቤቱ ውስጥ እንኳን ባይኖር ለዘረፋ የመጣው ግለሰብ በጩኸቱ ሳቢያ ደንግጦ እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡
የተማሪ ዮርዳኖስ ፈጠራ ምንም እንኳን ለሁሉም የህብረተሰብ አካል ቢሆንም በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ምክንያቱም መሳሪያው ከሚያሰማው ድምጽ በተጨማሪ ከፍተኛ ብርሀን የሚለቅ በመሆኑ መስማት ለተሳናቸው ግለሰቦች ደግሞ በሚለቀው ብርሀን እንዲነቁ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም የቤታቸው ወይም የንግድ ተቋማቸው ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ነው። ሌላው ሰው በቤት ውስጥ ኖረም አልኖረም ዘራፊዎች ድምጹን ሰምተውና ደንግጠው እንዲመለሱ የማድረግ ሀይል አለው፡፡ ሌላው የተማሪ ዮርዳኖስ የፈጠራ ስራ የድምጽ ማዳመጫ(Earphone) ነው፡፡ በብሉቱዝ አማካኝነት ድምጾችን ከስልክ ለማዳመጥ ያገለግላል፡፡
ልጆች ተማሪ ዮርዳኖስ ሌላው ከሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች መካከል ሰው አልባ ማማሰያ አንዱ ነው፡፡ ይህንን የፈጠራ ስራ ሊሰራ የቻለውም ብዙ ጊዜ የሚማሰሉ ነገሮች በእጅ ሲማሰሉ የመፍሰስ ችግር ያጋጥማል፡፡ ፈጠራው ይህንንና ተመሳሳይ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ነው፡፡
ልጆችዬ ተማሪ ዮርዳኖስ የፈጠራ ስራዎችን የሰራው ከወዳደቁ ቁሳቁሶች፣ ከዲናሞ በተለይም አንድ ቴሌቪዥን ከሚጠግን ጎረቤቱ ከሚሰጠው ቁሳቁስ እንደሆነ ነግሮናል፡፡ የፈጠራ ስራውን እንዲሰራ ያነሳሳው ምክንያትም አካል ጉዳተኞች ሲዘረፉ ራሳቸውን መከላከል ሳይችሉ ሲቀሩ በማየቱ እንደሆነም ነው የነገረን፡፡
ልጆችዬ ታዲያ የፈጠራ ስራውን የሚሰራው ጊዜውን በመከፋፈል ጥናቱን በማይሻማበት ሁኔታ መሆኑንም ነው፡፡ ቤተሰቦቹ እና መምህራኖቹ በፈጠራ ስራው ውጤታማ እንዲሆን ያበረታቱታል፡፡ ወደፊትም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እንደሚሰራ ነው የገለጸልን፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አበበ ሽፈራው በበኩላቸው፤ በትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ተሰጥዖ ያላቸው ተማሪዎች እንዳሉ ነግረውናል፡፡ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብም በትምህርት ቤታቸው በፈጠራ ስራ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለማበረታታትና የውደድር መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ስለመሆናቸውም ገልጸውልናል፡፡
ልጆች ርዕሰ መምህሩ እንደነገሩን ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታችሁ በተጨማሪ ያላችሁን ተሰጥዖ ማውጣት እንዳለባችሁ መክረዋችኋል፡፡ ስለዚህ ልጆች መደበኛ ትምህርታችሁን ከመከታተል ጎን ለጎን ያላችሁን ተሰጥዖ አውጡ በአግባቡ አዳብሩ፡፡ መልካም የእረፍት ቀናት፡፡
በለይላ መሀመድ