
AMN-ግንቦት 23/2017 ዓ.ም
ሐማስ አሜሪካ ላቀረበችው ለአዲሱ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ሃሳብ ምላሽ ተጨማሪ 10 የእስራኤል ታጋቾችን እና የ18 ሟቾችን አስክሬን አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል።
ቡድኑ በስምምነቱ መሰረት እስራኤል በርካታ የፍልስጤም እስረኞችን ነፃ ታወጣለች ብሏል።
ከእስራኤል በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩ ተገልጿል።
ዋይት ሀውስ ሐሙስ እለት ፤ እስራኤል የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡትን አዲሱን የጋዛን የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት መቀበሏን እና ከሐማስ መደበኛ ምላሽ እየጠበቀች መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አዲሱ ስምምነት ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ሃማስ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ለማስፈታት በሁለት ደረጃ 10 በህይወት ያሉ ታጋቾችን እና የ18 ሟቾችን አስክሬን አሳልፎ እንደሚሰጥ ተገልጾ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
በዛሬው ዕለትም ቡድኑ 10 የእስራኤል ታጋቾችን እና የ18 ሟቾችን አስክሬን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ ነው የተነገረው።
በጋዛው ጦርነት በትንሹ 54 ሺ 381 ግለሰቦች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡