የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሐረር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ላይ የሚዲያ መስክ ምልከታ እያደረገ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የልማት ስራዎችን ለህብረተሰብ በመረጃ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም በሀገሪቱ እየተካሄዱ የሚገኙ የመንግስት የልማት ስራዎችን የማስተዋወቅ አላማ ያደረገ የሚዲያ የመስክ ምልከት በየጊዜው እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል።
በዚህ ዙር በምስራቅ ኢትዮጵያ በማተኮር በሐረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሀረርጌ ዞን እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የልማት ስራዎች ላይ ቅኝት በማድረግ የሚከናወን መሆኑ ተጠቅሷል።
በመስክ ምልከታው በተለይም የአካባቢ ጥበቃ፣ የበጋ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ እና የገጠር ኮሪደር ልማቶች ዋነኛ የትኩረት መስኮች ይሆናሉ ነው የተባለው።
በዛሬው እለት በሐረር ከተማ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት፣ የሌማት ቱሩፋት እና የጅጎል ቅርስ እድሳት ስራዎች ምልከታ እንደተደረገባቸው ተጠቁሟል።
የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋን ለኑሮ ምቹ በማድረግ ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይ የሐረር ከተማን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ የሀረርን መልኮች ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው ተብሏል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት የሐረር ኮሪደር ልማት የከተሞች እድገት ካለፈ ታሪካቸው ጋር በተስማማ መልኩ መሄድ እንደሚችል ያሳየ ነው ማለታቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።