መልሶ የሚከፍለን ዋጋ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ ገጽታዋ እያማረ ነው፡፡ አፍንጫን የሚሰነፍጥ ሽታ የነበረባቸው አካባቢዎች አሁን የመዝናኛ አማራጭ በመሆን ሰዎችን ከመግፋት ወደ መጥራት ተሸጋግረዋል፡፡ የተጎሳቆሉ እና አይደለም ለነዋሪዎች ለእንግዶች እንኳን ምቹ ያልነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ የውበትንም፣ የምቾትንም ጸዳል ተላብሰዋል፡፡ ፕሮጀክቶች የሚጀመሩበት ብቻም ሳይሆን በፍጥነትና ጥራት ተገንብተው ወደሚጠናቀቁበት አዲስ ልምምድ ተሸጋግሯል፡፡ መዲናዋ ይህን እየከወነች ያለችው በራሷ በምትሰበስበው ገቢ መሆኑ ደግሞ ትርጉሙን ትልቅ ያደርገዋል፡፡

መዲናዋ ገቢን የመሰብሰብ አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ ለዚህ በቅርቡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ያቀረቡትን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት በማሳያነት ማንሳት በቂ ነው። መረጃው እንደሚያመላክተው በ6 ወራት 125 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 111 ነጥብ 5 (90%) ገቢ ተሰብስቧል። የገቢ አሰባሰቡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 74 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ37 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር (በ50%) እድገት አሳይቷል። ከዚህ በላይ ለመሰብሰብ የገቢ ማግኛ አማራጮችን አሟጥጦ መጠቀም እንዲሁም ገቢ የሚያሳጡ በሮችን መዝጋት ከመንግስት አካላት ብቻም ሳይሆን ህዝቡን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ መካከል የግብይት ስርዓቶች በደረሰኝ እንዲከወኑ ማድረግ ላይ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አምባሳደር ተካ (ዶ/ር) ይባላሉ። በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ማለትም፤ በትራፊክ አደጋ እና ወንጀል መከላከል እንዲሁም ከገቢዎች ቢሮ ጋር በመተባበር ለግብር ከፋዩ እና ለሸማቹ ማህበረሰብ ግብይትን በደረሰኝ መፈጸም እንደሚገባ ግንዛቤ መፍጠር ከጀመሩ ከሰባት ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡

ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ ከተማን ብሎም ሀገርን ማልማት የአንድ አካል ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ዜጋ ርብርብ ይፈልጋል፡፡ ሀገርን በማልማትና በመቀየር ሂደት ውስጥ አሻራ ማኖርን የመሰለ ነገር የለም ብለዋል፡፡

ይህን አሻራ የማሳረፍ እድል ከሚሰጡ ተግባራት መካከል  ግብይቶችን በደረሰኝ ማካሄድ አንዱ ነው፡፡ ራሳችን ስንገዛም ሆነ ሌሎች ሲገዙ ግብይቱ ያለደረሰኝ እንዲሆን መፍቀድ ልማትን የማደናቀፍ ያክል መቁጠር ይገባል፡፡ ይህን ከማድረግ አንጻር ሚናችን ምን ይመስላል? የሚለውን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ 

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት፣ በተለምዶ 72 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የመገበያያ ማዕከል ውስጥ እቃዎችን ሲሸምቱ ያገኘናቸው አቶ መንገሻ ብሩ፤ ለገዟቸው እቃዎች ደረሰኝ የመቀበል ልምድ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ፤ አንዳንድ ቦታ “ደረሰኝ የለንም” በማለት ነጋዴዎች ክፍተቱን ለራሳቸው ጥቅም የማዋል ነገር እንዳስተዋሉ ተናግረዋል፡፡

“በሰለጠነው ዓለም አንድ ግለሰብ እቃዎችን ሲሸምት ለእያንዳንዷ እቃ ደረሰኝ ካልያዘ፣ ድንገት መንገድ ላይ ፖሊስ ቢፈትሸውና ያለደረሰኝ ግብይት መፈፀሙ ቢታወቅ ሻጩም ሆነ ነጋዴው በህግ ከመጠየቅ አይድኑም፡፡ በደረሰኝ ግብይት ቢደረግ ጥቅሙ ለሀገር እና ለህዝብ ነው፡፡ ይህን በመረዳት ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል” የሚል እምነት እንዳላቸውም ነግረውናል፡፡ 

ህጋዊ የሆነ የደረሰኝ ግብይት በአግባቡ ማድረግ መቻል ለልማት ስራዎች በተለይም መንገድ ስራ፣ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ውሃ ልማት፣ ጤና ጣቢያ ግንባታ እና መሰል ሀገራዊ የልማት ስራዎችን ለመስራት ታስቦ በመሆኑ ለሸማቹ ብሎም ለነጋዴው ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እንደሚሰጥ በጎ ፈቃደኛው አምባሳደር (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

አምባሳደር (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ብዙ ጊዜ የትኛውንም አይነት እቃ ሲገበያዩ ሁሉም ባይባልም አንዳንድ ነጋዴዎች ደረሰኝ ለመስጠት ፍላጎት የላቸውም። ለተገበያዩበት እቃ ተገቢውን ክፍያ ከእነ ታክሱ ከከፈሉ ለመንግስት መድረስ ያለበትን ዋጋ ህጉ በሚያስቀምጠው መሰረት ምንም ሳይጭበረበር መከፈል እንዳለበት ያላቸውን ዕውቀትና ግንዛቤ በተግባር ለመግለፅ ጥረት ያደርጋሉ።  ይህን ግንዛቤ ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም እንዲተገብሯቸው ማድረግ ችለዋል፡፡  በመንግስት፣ በነጋዴው እንዲሁም በሸማች ማህበረሰብ በኩል ያለውን ክፍተት በሚገባ በማጤንም ከገቢዎች ቢሮ ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን አዘጋጅተው ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

“አገልግሎት ለመጠቀም የመጣ ሰው ደረሰኝ መጠየቅ አለበት፡፡ ነጋዴውም ዓመታዊ ግብር ሲከፍል ደረሰኞቹን ሰብስቦ ከጠቅላላ ክፍያው ላይ ተቀናሽ ማስደረግ ይችላል። በዚህ ልክ ስራዎች ከተከናወኑ ግለሰቦች ጋር በህገ ወጥ መንገድ የሚከማቸውን ገንዘብ በማስቀረት በርካቶችን በልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ መስራት ይቻላል” ሲሉም አምባሳደር (ዶ/ር) ተናግረዋል ፡፡

እርሳቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራቸውን በሚሰሩበት አካባቢ በተለይም ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ባለበት እንደ መርካቶ ባሉ ስፍራዎች የጅምላ አከፋፋዮች ለሸጡት እቃ ከዋጋ በታች (under voice) ደረሰኝ በመስራት ለነጋዴው ይሸጣሉ፡፡ ለገዢው አካል ደግሞ በትክክለኛው ዋጋ በመሸጥ ትርፍ ወደራስ የማስገባት ስራ ሲሰራ አስተውለዋል፡፡ በዚህ መሃል መንግስት ማግኘት የሚገባውን የገቢ ግብር ሳያገኝ፣ ህዝብም በተባለለት የደረሰኝ ግብይት ሳይስተናገድ ነጋዴው ብቻ እንዲከብር የሆነበትን አግባብ በማየት “ለምን?” በሚል ተነሳስተው ወደዚህ በጎ ተግባር እንደገቡም ተናግረዋል፡፡

እኛም በተለምዶ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ብለን ሲገበያዩ ያገኘናቸውን ወይዘሮ መንበረ መንግስቱን አነጋግረናቸዋል፡፡ ወይዘሮዋ በአስተያየታቸው፤ “ለመግዛት የፈለኩት ምንጣፍ ዋጋ የአስራ አምስት ሺህ ብር ነው፡፡ ታድያ በዋጋ ከተስማማን በኋላ ደረሰኝ ስጠይቅ ደረሰኝ እንደሌለው፣ በዋጋ ከተስማማሁ ያለደረሰኝ  ካልሆነ እንድተው ነገረኝ። እኔም በሀሳቡ ስላልተስማማሁ ሌሎች ሱቆች ላይ በማፈላለግ ለመግዛት ችያለሁ።

በደረሰኝ ግብይት ማድረግ ለገዛነው እቃ ዋስትና ብሎም ህጋዊ ስለመሆናችን ማረጋገጫ በመሆኑ ማንኛውም ሰው የትኛውንም አይነትና መጠን ሲገበያይ ግብይቱን በተስተካከለ መንገድ መከወን ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

በደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ እንዳሉ ሁሉ ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ ሻጭ እና ገዢዎችም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ናቸው፡፡ ይህ ገቢን ብቻም ሳይሆን ልማትንም ይጎዳልና መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

አቶ ፓርቲ ንጉሴ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመርካቶ ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ህግ ማስከበር ምክትል ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ “እንደሚታወቀው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ መርካቶ ነው፡፡ ሸማቹ ደረሰኝ መቀበል እንዲሁም ነጋዴው ደግሞ ደረሰኝ መስጠት ላይ ከፍተኛ ክፍተት ነበረው፡፡ ግብይቶችን በደረሰኝ ማድረግ መቻል በዋናነት ለህግ ተገዢ መሆንን ያሳያል፡፡ ነጋዴው ማህበረሰብ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሽያጭን በደረሰኝ ማድረግ ላይ በጣም ውስንነቶች ነበሩበት” ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ፓርቲ ገለፃ፤ ግብይቶችን በደረሰኝ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በዋናነት የግንዛቤ ስርፀት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ይህንን ስራ መስራት የሚችሉ ጠንካራ ሰራተኞችን የማሰማራት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም ደግሞ ቁጥራቸው ወደ 70 የሚጠጉ የዩንቨርሲቲ ምሩቃን አዳዲስ ሰራተኞች ስምሪት በመስጠት የማስተማሩን ስራ በስፋት እየከወኑት ይገኛል፡፡

እነዚህ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ያስገኙትን ውጤት ሲያስረዱም ተደራሽነትን የማሳደግ ስራ ተሠርቷል። ይህም ማለት ከዚህ ቀደም በነበረን የሰው ሃይል መድረስ ያልቻልነውን በእነዚህ ባለሙያዎች አማካኝነት የግንዛቤ ማስረፅ ሥራው ላይ በስፋት ለመድረስ እንዲቻል እድል ፈጥረዋል፡፡ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ገቢው እንዲያድግ አግዟል፡፡ በተለይም ከቫት የሚሰበሰበውን ገቢ በተመለከተ የሥስት ወር አፈፃፀም ብናይ እንኳን  በህዳር ወር 38 ሚሊዮን ብር፣ በታህሳስ ወር 40 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንዲሁም በጥር 67 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል።  ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መስክ ላይ ባለሙያዎች ወጥተው የሰሩት የግንዛቤ ስርፀት እንዲሁም የቁጥጥር ስራ ትልቁን ድርሻ ይይዛልም  ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ የደረሰኝ ግብይትን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ “በደረሰኝ የሚፈጸም  ግብይት ስንል የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ታክስ ከፋይ ከደንበኞቹ ጋር ለሚያከናውነው  ግብይትና  ለሚሰበስበው ገንዘብ እውቅና የሚሰጥ ሕጋዊ ሰነድ ነው። ግብር ከፋዩ ለደንበኞቹ ደረሰኝ ቆርጦ በመስጠት በመንግስት የተጣለበትን ግብር የማስከፈል እና የመክፈል ግዴታውን የተወጣ ስለ መሆኑ የሚረጋገጥበት የማረጋገጫ ወረቀት ነው” ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሰውነት ገለፃ፤ በከተማዋ ላይ የሚከናወን የትኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በደረሰኝ እንዲፈፀም ለማድረግ አስቻይ የሆኑ ሁኔታዎችን በሙሉ በመጠቀም ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከህዳር 1 ቀን ጀምሮ ቁጥራቸው ከ200 በላይ የሚሆኑ በቢዝነስ፣ ኢኮኖሚክስ፣ አካውንቲንግ እና ማኔጅመንት የትምህርት መስክ ያጠናቀቁ የዩንቨርስቲ ምሩቃን ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ወደ ሥራ የገቡት ምሩቃኑ  ከስራቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ስልጠና በመውሰድ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲከናወን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዋናነት ግብይቶች በደረሰኝ ስለመከናወናቸው ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡

አቶ ሰውነት አክለውም፤ ነጋዴውን ማህበረሰብ ለምን ካለደረሰኝ ግብይት አከናወንክ ብሎ ከመቅጣት ይልቅ የግንዛቤ ደረጃውን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሰረት በበጀት ዓመቱ ቁጥራቸው 6ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከብሎክ እስከ ቀጠና ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን አግኝተዋል፡፡ በሚፈለገው ልክ ሁሉም በደረሰኝ ግብይት መከወን ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል ቀጣይ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

አዲስ አበባ በሚጠበቅባት ልክ ገቢዋን ለመሰብሰብ ቢሮው የቁጥጥር ባለሙያዎችን ሰማንያ በሚሆኑ ብሎኮች በማደራጀት ጠዋት፣ ከሰዓት እንዲሁም በማታው ክፍለ ጊዜ ግብይቶች በደረሰኝ ስለመከናወናቸው ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተሰራው ስራ የተገኘውን ውጤት አቶ ሰውነት ሲናገሩ፤ በግልፅ ያለደረሰኝ ሽያጭ የሚያከናውን የለም። ደረሰኝ አለመቁረጥ ወንጀል መሆኑን በመረዳት አብዛኛው ነጋዴ ህጋዊ የሆነውን ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ገዢውም አካል “ደረሰኝ ስጠኝ” በማለት ግብይቱን ይከውናል፡፡ ከማዕከል እስከ ወረዳ በገቢዎች ተቋማት የሚስተዋሉ ከደረሰኝ ግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችና የሌብነት ድርጊቶች በነፃ የስልክ መስመር 7075 ጥቆማ ያደርሳሉ፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ያለ ደረሰኝ ሲሸጥ የተገኘ ነጋዴ 100 ሺህ ብር ይቀጣል። ቅጣቱ ድግግሞሽ ሲኖረው ደግሞ ከንግድ እንቅስቃሴ እስከ ማስወጣት ይደርሳል፡፡ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ያለደረሰኝ ግብይት ባከናወኑ 3 ሺህ 857 ነጋዴዎች እና የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ከገንዘብ ቅጣት ባሻገር ክስ የተመሰረተባቸው የንግዱ ማህበረሰቦች መኖራቸውን ተከትሎ ቢሮው ከቅጣት 297 ሚሊዮን በላይ ብር ሰብስቧል። 839 በሚሆኑት ላይ ደግሞ ክስ ተመስርቷል፡፡ አሁንም አሰራሩን አጥርቶ ለመሄድ ያስችል ዘንድ ያለ ደረሰኝ ለመሸጥ የሚሞክሩ አምራች፣ አስመጪና አከፋፋዮች ካሉ ማህበረሰቡ የመጠቆም ሃላፊነት አለበት፡፡ ማህበረሰቡም ቢሆን የትኛውንም አይነት እቃ ሲገዛ ደረሰኝን በመቀበል የከተማዋን ገቢ ለመጨመርና ንግዱን ሥርዓት ለማስያዝ የሚደረገውን ጥረት መደገፍና ህገ ወጦችን መከላከል ይኖርበታል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review