AMN – የካቲት 30/2017 ዓ.ም
መሬት ባንክ የገባ መሬት በመውረር በተገነባ ግንባታ ላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 2 መሬት ባንክ ገብቶ ሲጠበቅ የነበረ 1000 ካ.ሜ. የህዝብና የመንግስትን መሬት በህገወጥ መንገድ ሁለት ግለሰቦች የ2012 ዓ.ም ካርታ አለን በማለትና ከወረዳው የግንባታ ፍቃድ በማውጣት ቦታውን አጥረው ህገ-ወጥ ግንባታ ለመገንባት ሙከራ ሲያደርጉ መያዛቸውን የባለስልጣን መስርያ ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ባለስልጣኑ መሬት ባንክ ገብቶ ሲጠብቀው በነበረን መሬት ላይ የተገነባውን ግንባታ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ደንብ ማስከበረ ጽ/ቤት ከክፍለ ከተማና ከወረዳ አመራሮች ጋር በመቀናጀት የጸጥታ አካላትን በማሳተፍ ግንባታውን በማፍረስ የመንግስትና የህዝብ መሬት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ማድረጉ አስታውቋል።
ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ መረጃውን በማደራጀት በሊዝ አዋጁ ተጠያቂ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁሟል።
ባለስልጣኑ በህገ-ወጦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡
ደንብ የሚተላለፉ ግለሠቦችን የከተማዋ ነዋሪዎች በ9995 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡