መሶብ የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ሪፎርማችን አንዱ መሠረት ነው – አቶ ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing መሶብ የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ሪፎርማችን አንዱ መሠረት ነው – አቶ ተመስገን ጥሩነህ

AMN ሚያዝያ 24/2017

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት መሶብ የሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ሪፎርማችን አንዱ መሠረት ነው ብለዋል፡፡

የመንግስትን የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ፣ ለማፋጠን ብሎም የተቋማት ግንባታን ለማጠናከር ማዕከሉ ትልቅ አቅምን ይፈጥራል፡፡ ለዓመታት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት በመንግስት በኩል ለሚደረገው ጥረትም ወሳኝ እርምጃ ነው።

መሶብ ውብና ምቹ የሥራ ከባቢ፣ ሀገር በቀል የአገልግሎት ማሳለጫ የቴክኖሎጂ ስርዓትን ያሟላ እንዲሁም ሙያዊ እውቀትና ክህሎትን በተላበሱ ወጣት አገልጋዮች የሚመራ ነው።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ጎታች የቢሮክራሲ ሂደቶችን በመቀነስ፣ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ፣ ለኢንቨስትመንትና ንግድ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት እና መዳረሻችን ለሆነው ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል።

መሶብ የመሰባሰብ፣ የመካፈል እንዲሁም የመደመር በረከት ህያው አብነት ነው። ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የታላቁ ጉዟችን አንድ ደማቅ ዘርፍ ነው። አገልግሎትን እያዘመንን ቅሬታዎችን እየፈታን ከሀገር የተሻገረ ምሳሌ የሚሆን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ዕውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review