AMN-መጋቢት 11/2017 ዓ.ም
“መሶብ” የተሰኘ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የሚያስችል አሰራር በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራርያ ፤ “መሶብ ” የተሰኘ የአንድ መስኮት አገልግሎት በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ እና ፕላን ኮሚሽን እና ሌሎች ተቋማት በጋራ እየሰሩበት ያለው ይህ አሰራር በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አሁን የሚጀምረው የ “መሶብ” አገልግሎት በአንድ ቦታ ለ 8 ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች እና ከ 20 በላይ አገልግሎቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አሰራሩ በሂደት ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከአንድ ቦታ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሲስተሙ በሀገር ልጆች መገንባቱን እና ቦታ ተዘጋጅቶ ስልጠና ተሰጥቶ ስራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡
ስራው ሲጠናቀቅ ለሀገር ትልቅ ብስራት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡