ከኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ
ከዚህ በፊት አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን መንግሥት ያሳውቃል።
ሀገራዊ ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን የላቀ ሚና መንግሥት ስለሚረዳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዲፈታ መንግሥት የመሪነቱን ሚና መጫወቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ግንባታ የነበራትንና የሚኖራትን ሚና በመገንዘብ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህ አቋሙም ይቀጥላል።
ይሄንን ያልተረዱ አንዳንድ አካላት ችግሮችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም እንኳን፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያንዋ እና ለምእመንዋ ሲል በሆደ ሰፊነት ለማለፍ ወስኗል። ይሄም ከግለሰቦች ችግር ይልቅ የቤተ ክርስቲያንዋን አስተዋጽዖ ስለሚመለከት ነው።
መንግሥት ችግሩ እንዲፈታ ሲኖዶሱ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሏል። በሂደቱም ተቀራርቦ መነጋገር ከሁሉም የተሻለ የመፍትሔ መንገድ መሆኑ ታይቷል።
ስለዚህም ሲኖዶሱ መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት እንዲመለከተው በጠየቀው መሠረት፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሲኖዶሱ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ እንደሚያደርግ ይገልጣል።