መንግሥት ጎንደር በታሪኳ ልክ የዕድገት መሻቷን እንድታሳካ አበክሮ እየሠራ ነው- ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

You are currently viewing መንግሥት ጎንደር በታሪኳ ልክ የዕድገት መሻቷን እንድታሳካ አበክሮ እየሠራ ነው- ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

AMN-ጥር 10/2017 ዓ.ም

መንግሥት ጎንደር በታሪኳ ልክ የዕድገት መሻቷን እንድታሳካ አበክሮ እየሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ታየ በወቅታዊ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጎንደር በኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ ስርዓተ መንግሥትና ሀገር ግንባታ ጉልህ ስፍራ አላት ብለዋል።

ለዚህም አብያተ-መንግስታቱን፣ ቀደምት ቅርሶችንና ቅድመ አያቶች ለሀገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማሳያነት አንስተዋል።

የአሁኑ ትውልድም የቀደሙ አባቶችን አርቆ አሳቢነትና ጥበብ በመያዝ የተገኙ ድሎችን ማስቀጠልና ሰላምን ማፅናት ላይ በአርዓያነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር ህዝብ ለዘመናት ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎች በተጨባጭ ምላሽ እንዲያገኙ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግስት ጎንደር በታሪኳ ልክ የከፍታና የዕድገት መሻቷን እንድታሳካ በሁሉም መስክ አበክሮ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሆኖም የጎንደር መለወጥና የህዝቡ በልማት ተጠቃሚ መሆን የማይፈልጉ አንዳንድ አካላት አካባቢው ሰላም እንዳያገኝ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር አውስተዋል።

ይህን መጥፎ አካሄድ ቀድሞ የተቃወመውና ያከሸፈው የጎንደር ህዝብ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ በመሆኑም ሰላምና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በጋራ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ችግሮች ሲኖሩ በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ባህልን በማጎልበት መፃኢ ዕድሎችን በጋራ መተለምና ማሳካት የትውልዱ ኃላፊነት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review