AMN_የካቲት 18/2017 ዓ.ም
የብሔራዊ እና ክልላዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረቶች የ2017 ዓ.ም የግማሽ ዓመት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመድረኩ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት
በዚህም ወቅት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ህግ እና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ፣ መንግስት ፍልሰት ችግር ሳይሆን በአግባቡ ሊመራ የሚገባው ኩነት መሆኑን እንደሚያምን ገልፀዋል፡፡
አክለውም የትብብር ጥምረቱ በአዋጅ የተጣሉበትን ተግባር እና ኃላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል የፍልሰት ዋና ዋና የትኩረት መስኮችን መሰረት በማድረግ በስሩ ስድስት የሥራ ቡድኖች በህግ እንዲደራጁ የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የስራ ቡድኖቹን ጨምሮ የትብብር ጥምረቱን እንቅስቃሴ የሚደግፍና የሚያስተባብር ጽ/ቤት በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ እንዲቋቋም ተደርጎ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
በክልሎችም በተመሳሳይ የትብብር ጥምረት አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ በበኩላቸው በሰው መነገድ፣ ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቀነስ የሚቻለው ለችግሩ ገፊና ሳቢ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መንስኤዎችን በመቅረፍ ረገድ በትኩረት ሲሰራ እና መደበኛ ፍልሰትን ለማሳለጥ አስቻይ የሆኑ የህግ እና የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት ሲቻል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሀገራችን ከፍልሰት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች መከላከል፣ ለተጎጂዎች እንክብካቤና ድጋፍ በማድረግ በፍልሰት ሂደት የሚከሰቱ ስጋቶችን በመቀነስ ፍልሰት ይዟቸው የሚመጡ መልካም እድሎችን ደግሞ ለሀገር ልማት ለማዋል በተለያዩ ሥምምነቶች እና በህገ-መንግሰቱ ድንጋጌዎች የተጣለባትን ግዴታ ለመወጣት የተለያዩ የህግ እና የተግባር እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ሀገራችን ፍልሰትን የሀገር ደህንነት፣ ልማትና ብልጽግና እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መከበርን ባረጋገጠ መልኩ ለመምራት እና ለማስተዳደር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት መግለፃቸውን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡