መንግስት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

AMN-ግንቦት 07/2017 ዓ.ም

መንግስት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋዬ ጎበዛይ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ይበልጥ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም የበጋ እና የበልግ ወቅት የግብርና ሥራዎችን፣ የስንዴ ምርታማነትን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎችን እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭን ጠቅሰዋል፡፡

የውሃ አማራጮችን አሟጥጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለበጋ ስንዴ 4.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማቱን በመግለጽም ፤ ከዚህ ውስጥ 3.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ ከ66 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

የበልግ አዝመራ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎችም 2.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን በማንሳት ከዚህም ውስጥ 235 ሺህ ሄክታር መሬቱ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review