የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ሰራዊቱ የምስራቅ አፍሪካን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚንስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የ10 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።
በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ እንድታገኝ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት እና በጋራ ለመበልፀግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አቅደን ነው ብቃት ያለው የባህር ኃይል የገነባነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሁን ላይ በየብስም ሆነ በባህር የሚቃጡ ትንኮሳዎችን የሚመክት ስራዊት መገንባቱን አስገንዝበዋል፡፡
ኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው የሰራዊቱን አስተማማኝ የሎጂስቲክ ክምችት ማሟላት እንደተቻለ ገልፀው ከ54 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውሰጥ ተዋጊ ሀይሎችን በሰላም ተቀብሎ የተለያዩ ስልጠናዎችን ከሰጠ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል እንደቻለ አብራርተዋል፡፡