AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዕድሜ ያላት የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና ናት፡፡
ከኒውዮርክ እና ጀኔቭ ቀጥሎ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደሆነች ለዓመታት ሲነገር የቆየ ሀቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ ተሰሚነት እያደገ መምጣት፣ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ዘርፍ እየታየ ያለው መሻሻል የአፍሪካ መዲናዋን የበርካቶችን ቀልብ እንድትስብና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማእከል እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የመዲናዋ በኮሪደር ልማት በእጅጉ መለወጥና የመሠረተ ልማቶቿ መዘመን፣ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም ያሉ ከሙዚዬም ባሻገር ሰፊ መሠረተ ልማት የያዙ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ደግሞ የእንግዶችን ቆይታ አስደሳች አድርገው ዕርካታቸውን እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹና ተመራጭ እየሆነች መጥታለች፡፡ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በአዲስ አበባ በብዛት እየተካሄዱ ነው፡፡ የመንግሥት የዲፕሎማሲ አቅም እየጎለበተ መምጣትና ከተማዋ በሁለንተናዊ ፈጣን ለውጥ ውስጥ መገኘት ለመድረኮቹ መምጣት ሚናው የላቀ ነው፡፡
በፍጥነት እየተለወጠ ከመጣው የመሰረተ ልማት እድገትና በዲፕሎማሲ ረገድ ከተመዘገቡ ድሎች በተጨማሪ ምቹና ለጤና ተስማሚ የአየር ሁኔታ መኖር፣ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና እየዘመነ የመጣና ባህላዊ እሴቶችን ያካተተ መስተንግዶ፣ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም መኖር አዲስ አበባን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው።
በዚህም የተነሰ በያዝነው ወር ብቻ ወደ 30 የሚጠጉ በርካታ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎች በአዲስ አበባ በስኬትና በድምቀት ተካሂደዋል፡፡
በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዙሪያ የመከረው የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ፣ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበር ጉባኤ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባኤ፣ ዓለማቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ኮንፈረንስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት (UNIDO) ጉባኤ፣ የዩኒስኮ (UNESCO) በጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መከላከል ቀን መታሰቢያ እና ሌሎችም በርካታ መድረኮች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፡፡
በዚህም መዲናችን ከአህጉር መዲናነት ባሻገር የዓለም የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን እየተሠራ እንደሚገኝ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በአንድ ወቅት አዲስ አበባ በውበቷና በመሰረተ ልማት ወደኋላ የቀረች በመሆኗ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችን ለማስተናገድ አትመጥንም ተብላ የተዘመተባት ከተማ በተሰራው ሥራ ሌሎች ሀገራት በዓመታት ውስጥ እንኳን ለማዘጋጀት የማይችሉትን ትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በተሳካና በደማቅ ሁኔታ ለማስተናገድ በቅታለች። እነዚህ ዓማቀፍ ኹነቶች የከተማይቱን ብሎም የሀገሪቱን ገጽታ አጉልተው ያሳያሉ፡፡
ከቱሪዝም ኮንፈረንስ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም የጎላ ነው፡፡
ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ሚናው የላቀ ነው፡፡ አዳዲስ ወደ ሥራ የገቡ ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ ተጨማሪ ገቢና ዐቅም ይፈጥራል።
ለመዲናችን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማደግ የነዋሪው ሰላም ወዳድና ሰላም ጠባቂ መሆን የላቀ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህንን የከተማዋን ነዋሪዎች ሰላም ወዳድነትና ለሰላም ዘብ የመቆም በጎ ልምድ መንግሥት ዕውቅና ይቸረዋል፡፡
አሁንም የሰላም ጠበቃነቱን አጠናክሮ በማስቀጠል አዲስ አበባን ከዓለማችን ቀዳሚ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል እንድትሆን የተለመደ ጥረቱን ሕዝቡ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት