ለክረምት መርኃ ግብር በከተማዋ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ችግኝ መትከልና የደን ልማት ስራ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ አስቆጥሮ እስካሁንም ተከላው ቀጥሏል፤ ነገር ግን አሁንም ሰፋፊ መሬቶች አፈር ተራቁተው መመልከት የተለመደ ነው። በየጊዜው የሚጀመሩ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችም ወጥነት ያልነበራቸውና ሳይንሳዊ አሰራሩን የተከተሉ ስላልነበር ከተሞች ጭምር ውበትና ጽዳታቸውን ማስጠበቅ ተስኗቸው ቆይተዋል፡፡
ይሁንና የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከሰባት ዓመት በፊት ከተጀመረ በኋላ በሀገር አቀፍ በአዲስ አበባ ደረጃ ችግኝ መትከል የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቶ የተራቆቱ መሬቶች እልባት እያገኙ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥንም በዘላቂነት ለመከላከል ስራዎች በቋሚነት እየተሰሩ ይገኛል፡፡ በተከላ መርሃ ግብሩም በተለይ የመሬት ለምነትን የሚጨምሩ ሀገር በቀል እፅዋቶች ላይ ትኩረት የሚደረግ ሲሆን ይህም የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማድረግ ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የሱሲኒ ችግኝ ጣቢያ አስተባባሪና የግብርና ባለሙያ አበበች መካ ችግኝ ጣቢያው በከተማ አስተዳደሩ ስር ካሉ ችግኝ ጣቢያዎች ትልቁ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ ለአንድ መቶ ሴቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም ሌላ ለዘንድሮው የክረምት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 1 ሚሊየን 6 መቶ ሺህ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በችግኝ ጣቢያው የውበት፣ የጥላ፣ የፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ አራት አይነት ዝርያ ያላቸው ችግኞችን የማፍላትና የመንከባከብ ስራ እየተሰራ እንደሆነ የገለፁት አስተባባሪዋ ለጥላ ከሚሆኑ ሀገር በቀል ዝርያዎች ወይራ፣ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨት፣ ኮርች የአበሻ ፅድና መሰል ችግኞች በብዛት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
መጤ ወይም የውጭ ዝርያ ከሚባሉት የጥላ ችግኞች መካከል ደግሞ የአካባቢን ስነምህዳር የማይጎዱ እንደ ሽውሽዌ፣ ግራቪሊያ፣ ጃካራንዳ፣ ሳሊግና፣ አኬሻ፣ ኦሜድላ እና ዲከረንስ ተጠቃሾች ናቸው።
ከፍራፍሬ ዝርያዎችም አቡካዶ፣ ማንጎ፣ አፕል፣ ሎሚ፣ ብርቱካን እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን በማፍላት ከአዲስ አበባ አልፎ እንደሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትኛውም ችግኝ አድጎ ዛፍ እንዲሆን በችግኝ ተከላ ወቅት ማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል የሚሉት የግብርና ባለሙያዋ በችግኝ ጣቢያው ለችግኝ የሚደረገው እንክብካቤና ከወጣ በሆላ ያለው እንክብካቤ እጅጉን እንደሚለያይ በተለይ በተከላ ወቅት የሚታየው ቸልተኝነት እንደሚያሳዝናቸው ነው የተናገሩት፡፡
አልፎ አልፎ ችግኞቹን እስከታሸጉበት ላስቲክ ከመትከል ጀምሮ ሳይተክሉ ጥሎ የመሄድ ሁኔታ ሊስተካካልና ሊታረም ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ችግኝ ተካዩ ማህበረሰብ ዛፎች ከሌሉ የሰው ልጅ እንደማይኖር በማሰብ በችግኝ ተከላ ወቅት የታሸጉበትን ላስቲክ ቀደው በበቂ ሁኔታ አፍር አልብሰው መትከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ መንግስቱ በበኩላቸው የሁለተኛው ዙር ሁለተኛ ምዕራፍ ሰባተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በዘንድሮው የክረምት ወቅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አዲስ አበባ ከተማ እየተደረጉ ባሉ ዝግጅቶችም ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ የቦታ ልየታ ስራ እየተሰራ ሲሆን በከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ደረጃ ብቻ የጥላ፣ የውበት፣ የፍራፍሬ እና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ወደ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ አስተያየት ቢሮው በከተማ ደረጃ ያቋቋማቸው አስራ እንድ ችግኝ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን እንዲሁም አመቺ በሆኑና በየወረዳው ባሉ የትምህርት ተቋማትም ችግኝ የማፍላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በዚህም አራት አይነት ዝርያ ያላቸውን ወደ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን የሚጠጉ ችግኞችን ማፍላት መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡ ቸግኞቹ ለተክል ከደረሱ በኋላ የት ነው የሚተከሉት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ በ119 ወረዳዎች ወደ 1 ሺህ 571 የሚሆን የቦታ ልየታ ስራ ተሰርቷል፡፡
መርሃ ግብሩ እንደአጠቃላይ ወደ 594 ሄክታር በሚሸፍን መሬት ላይ እንደሚከናወን ያስታወሱት ወይዘሮ ስንታየው በዚህም 40 በመቶ የጥላ፣ 40 በመቶ የውበትና 20 በመቶ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ነው ያብራሩት፡፡
አዲስ አበባ በተለይ የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ሰፋፊ የአረንጓዴ ቦታዎች አሏት፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በመብራት ሃይል በኩልም የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የተተከሉና የመብራት መስመሮች ጋር ንክኪ በመፍጠራቸው የተቆረጡ ዛፎችንም ሊተኩ በሚችሉ በውበትና ጥላ ዛፎች የመተካት ስራዎች በክረምቱ መርሃ ግብር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
በተቆረጡት ዛፎች ምትክ የመንገድ ዳርቻ፣ አካፋዮችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ከመለየታቸውም ሌላ የሚተከሉ ችግኞችም ተዘጋጅተዋል፡፡ ስራውን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን ያስችል ዘንድም ከግንቦት 19 ጀምሮ ስራውን ለሚያከናውኑ ለወረዳ፣ ክፍለከተማና ባለድርሻ አካላት ስልጠና መዘጋጀቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ በዋናነትም በችግኝ ተከላ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ማስቀረትን ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ለአብነትም ጉድጓድ ሲቆፈር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ጥልቀቱና ስፋቱ ምን ያህል መሆን አለበት፣ የአንዱ ችግኝ ከአንዱ ያለው ርቀት ምን ያህል መሆን አለበት፣ ችግኞች ሲተከሉስ ምን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል በምን አይነት መልኩስ መተከል አለባቸው በሚሉት ላይ የሚያጠነጥን ስልጠና ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቢሮ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ በክፍለ ከተማ ደረጃ እየተሰራ ያለውን ስራ በየሳምንቱ ሀሙስ ክፍለ ከተሞችን የመገምገም ስራ ይሰራል ያሉት ዳይሬክተሯ እንደከተማ የአረንጓዴ አሻራ ስራ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከናወን እንደመሆኑ ስራው አዲስ ባይሆንም በየጊዜው እየታየ መስተካከል ያለበት እየተስተካካለ የፅድቀት መጠኑን አሁን ካለበት ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ችግኝ ተከላው ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ምህዳራዊ ለውጥ ማምጣት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል እየፈጠረ ያለም ዘርፍ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ስር ባሉ ችግኝ ጣቢያዎች ብቻ ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ የቦታ ዝግጅት ብሎም በተከላና እንክብካቤ ዘርፍ ለአምስት መቶ ወገኖች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡
የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ኮተቤ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ቅድስት ጌታቸው አንዷ ናት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሲሲኒ ችግኝ ጣቢያ ከ2015 ዓመተ ምህረት አጋማሽ ጀምሮ ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ ስራ ተቀጥራ እየሰራች እንደሆነ የምትገልፀው ወጣቷ በችግኝ ጣቢያው መስራቷ ከሰዎች ጋር ተግባብቶ በጋራ መስራት እንዴት እንደሚቻልና ስለችግኝ ምንነት፣ ዘር ወደችግኝነት እንዴት እንደሚቀየር ከመጀመሪያው ሂደት ጀምሮ እስከመጨረሻው ምን መሆን እንዳለበት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እውቀት እንዲኖረኝ አስችሎኛል ትላለች፡፡
ወጣት ቅድስት ጨምራ እንደምትገልጸው ነገ የተሻለ ኑሮ መኖር ያስችላት ዘንድ ቀን ቀን በችግኝ ጣቢያው ስራዋን ስታከናውን ውላ በማታው ክፍለ ጊዚ ደግሞ በዲግሪ መርሃ ግብር ማርኬቲንግ እየተማረች እንደሆነም ተናግራለች፡፡ ሰርታ እራሷን ማስተማር በመቻሏ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ እርካታ እንዳገኘች ትናገራለች፡፡
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ፅጌ ነጋም በችግኝ ጣቢያው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው እንስቶች መካከል ናቸው፡፡ በችግኝ ጣቢያው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑ ወደ ሁለት አመት እንደሚጠጋ ጠቅሰው በቆይታቸውም ችግኝ ከማፍላት ጀመሮ ለተከላ ዝግጁ እስከሚሆኑ ድረስ የእንክብካቤ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከዓመት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም እየታየ የፅድቀት መጠኑም እየጨመረ ነው የሚሉት የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ፣ ይህም የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት የመጣ መሆኑን ጠቅሰው አካባቢ ጥበቃ ባወጣው መረጃም እንደከተማ የፅድቀት መጠን 88 በመቶ መድረሱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ቢኖሩም ህብረተሰቡ ፀሐይ፣ ብርድና ዝናብ ሳይበግረው ችግኝ ለመትከል የመውጣቱን ያህል በመንከባከብ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸው ግን የሚካድ አይደለም፡፡ ይህንንም ድክመት በማስተካከል ህብረተሰቡ የተከለውን ችግኝ በመንከባከብ ረገድም መትጋት እንዳለበት ነው ዳይሬክተሯ ያሳሰቡት፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ