መዲናዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶችን አከናውናለች- ሎረንስ ፍሪማን

You are currently viewing መዲናዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶችን አከናውናለች- ሎረንስ ፍሪማን

AMN- ግንቦት 20/2017 ዓ.ም

በተደጋጋሚ አዲስ አበባን የማየት እድል ያገኙት የአፍሪካ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሎረንስ ፍሪማን፣ መዲናዋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተናግረዋል።

አዲስ አበባን የአፍሪካ አህጉር መንበርነቷን እና የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን በሚመጥን ልክ ለማልማት ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ረጅም ርቀት መኬዱንም አንስተዋል።

ፈተናና ውስብስብ ችግሮች ያልበገራቸው በፌደራል መንግስት እና በከተማ አስተዳደሩ በሚከናወኑ አያሌ የመልሶ ማልማት ስራዎች ለዘመናት ወይቦ የቆየው የመዲናዋ ገጽታ ማንፀባረቅ ጀምሯል ብለዋል።

የመዝናኛ አማራጮች የማይታሰቡባት ሰውና ተሽከርካሪ እኩል የሚጋፉባት አዲስ አበባ፣ አሁን በብዙ ተንፍሳ ሁሉም በየፈርጁ ስርዓትን ይዞ ካሰበበት ለመድረስ ማስቻሉንም አንስተዋል።

ልጆች በነፃነት እንዲቦርቁ አዛውንቶችም ሲያሻቸው እየተራመዱ አሊያም ተቀምጠው ሊያወጉ የሚችሉበት መደላድል ተፈጥሯል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ሳቢና ተመራጭ ለማድረግ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ሰው ተኮር ስራዎች ተከናውነዋል እየተከናወኑም ይገኛል።

ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራ በጠራና ባጠረ ጊዜ ጨርሳ ለተገልጋዩ ማስረከብ ባህሏ ያደረገችው አዲስ አበባ፣ አፍሪካን የሚወክሉ እንደ አደዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ ሌሎች ለከተማዋ ስምና ክብር የሚሚጥኑ ተቋማትን መገንባት መቻሏ ለራሷና ለአፍሪካ ኩራት ከመሆን ባሻገር የከተማዋን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እያነቃቁ መሆኑንም ሎረንስ ፍሪማን ተናግረዋል።

በመዲናዋ በመገንባት ላይ ያሉና ተገንብተው የተጠናቀቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶቿ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ህይዎት ያቃለሉ እና የኑሮ ዘይቤን ያዘመኑ ስለመሆናቸውም አመላክተዋል፡፡

በሔኖክ ዘነበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review