AMN – መጋቢት 5/2017 ዓ.ም
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዘመኑን በዋጀ መልኩ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከበሩ ስራዎች አተኩረው መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
ተለዋዋጭ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እና የጂኦ-ፖለቲካል አሰላለፍ በሚዲያ ስራዎች የሚኖረው አንድምታ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና ሆርን ሪቪው ከተሰኘ ኦንላይን ሚዲያ ጋር በመተባበር ተዘጋጅቷል።

የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ድሪባ፣ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ጥቅም በማስከበር ረገድ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅምን ፈጥራሉ ብለዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ፍላጎት መረዳት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የተሳሳቱ መረጃዎችን መዋጋት እና በእውነታ ላይ የተመሰረተ፣ በሚገባ የተጠና ዘገባዎችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዲጂታል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ፣ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዓለም እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ መያዝ አለባቸው ብለዋል።
በተለይም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮችን በመረዳት እና በመተንተን የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት በማስቀደም መስራት ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በሄለን ጀንበሬ