
መጽሐፍት ለትውልድ በሳምንት አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ጠቃሚ ናቸው ያልናቸውን መጽሐፍት ለእናንተ ለውድ ተከታዮቻችን የምንጋብዝበት አምድ ነው።
የመጽሐፍቱ ምርጫ የእናንተ የውድ ተከታዮቻችንም ጭምር ነው፤ አንብባችሁ የወደዳችሁትን መጽሐፍ ብትጠቁሙን እኛም አንብበን ያላነበቡ እንዲያነብቡት መልሰን እንጋብዛለን።
ለዛሬ “ትኩረት”ን በጨረፍታ ዳስሰን፤ ሙሉውን እንዲያነቡት ግብዣችን ነው። እነሆ!! ትኩረት
ርዕስ – ትኩረት
ደራሲ – ኢዮብ ማሞ (ዶ/ር)
ገጽ – 133
እንደ መጽሐፉ ከሆነ ትኩረት ማለት ለወቅቱ አስፈላጊ ነገር ሙሉ ሐሳብን የመስጠት ብቃት ማለት ነው።
መረጋጋት እና ማተኮር አለመቻል የሰውን የፈጠራ ብቃት የሚወስድ አንደኛ ጠላት ነው።
ይህንን ለማወቅ ከፈለጉ ደግሞ፣ ፀጥ ያለ አካባቢ ብቻዎን ሲሆኑ እና ከየቀኑ ኡደት ዘወር ብለህ ደስ የሚልዎትን ነገር እያደረጉ ሲረጋጉ የሚመጡልዎትን አዳዲስ ሐሳቦች አስታውሱ። ሲረጋጉ እና ሲያተኩሩ ብቻ ውስጥዎ አዳዲስ ነገሮችን ማፍለቅ ይጀምራል።
ዘመናዊነት እና ሥልጣኔ ብዙ የሰጠን መልካም ነገር የመኖሩን ያህል ሚዛናዊ ልውውጥ እንዳላደረገ ግን እሙን ነው። ጥቂት ሰጥቶን ብዙ ወስዶብናል። የመጫወት ብቃትን ሰጥቶን ለመጫወት ግን ያለንን ጊዜ ቀምቶናል።
ነገሮችን በቀላሉ እና በፍጥነት የምናከናውንባቸውን መሣሪያዎች ፈጥሮልን በዚያው “ፈጥነን” እንድንቀር እና የምንሠራውን ለማወቅ እንኳ ጊዜ እንዳይኖረን አድርጎናል።
በእጆቻችን ላይ የሚገኙትን ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች እኛ ልንጠቀምባቸው ሲገባን የሚጠቀሙብን እነሱ ናቸው። እኛ እነሱን ልናበራቸው እና ልናጠፋቸው ሲገባን እነሱ እኛን “ያበሩናል”፣ ብሎም “ያጠፉናል”፤ ስሜቶቻችን በእነሱ ላይ ተመሥርተዋልና።
አንድን ነገር ጀምረን ብዙም ሳንራመድ ሌሎች ሐሳባችንን የሚሰርቁ ነገሮች ብቅ የሚሉበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው። የጀመሩትን ለመጨረስ፣ ውጤት ከሌላቸው ነገሮች ዘወር በማለት በዋናው ነገር ላይ ለማተኮር እና ከአማካኝ ሰዎች ልቆ ለመገስገስ ትኩረት ወሳኝ ነው። የተሰበሰበ ትኩረት ያለው ሰው በአጭር ጊዜ ብዙ ርቀት መሄድ የሚችል ሰው ነው።
ይህ መጽሐፍ የትኩረትን ትርጉም እና ተግባራዊነት በግልጽ ያሳያል።
“የትኩረት ደረጃህን ለመመዘን የሚከተለውን መጠይቅ እንድትሞላ እና ውጤትህን እንድታካፍለን ልጋብዘህ” ሲል መጽሐፉ ይጠይቃል።
1. በቀጠሮዎች እና በስብሰባዎች በሰዓቱ የመገኘትህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰተዋለህ?
2. አንድን ሥራ ጀምሮ የመጨረስህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰጠዋለህ?
3. አንድን ለማከናወን ያሰብከውን ነገር ለሌላ ቀን ሳታስተላልፍ በእለቱ የመጀመርህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰተዋለህ?
4. የአንድን ተግባር ውጤት አስመልክቶ ግልጽ የሆነ ግብ የማውጣትህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰጠዋለህ?
5. በስብሰባ ወቅትም ሆነ ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ሐሳብህን ከሞባይል ስልክህ ላይ የማንሳትህን ሁኔታ (ሞባይልህን ደጋግሞ አለማየት እና አለመነካካት) ከአስር ስንት ትሰጠዋለህ?
6. ከኢሜል፣ ከፌስቡክ እንዲሁም እንደ ሞባይል እና ከመሳሰሉት ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ውጪ ካለምንም መጨናነቅ ለሰዓታት ተለይቶ የመቆየትህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰጠዋለህ?
7. ሰዎች ሲናገሩ ምን መልስ እንደምትሰጥ ከማሰብ ይልቅ ሙሉ ትኩረት ለሰዎች የመስጠትህን ሁኔታ ከአስር ስንት ትሰጠዋለህ? እያለ የቀጥላል። እናም ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት የትኩረትዎን መጠን ይለኩ።
መጽሐፉንም አንብበው ስለ ትኩረት ምንነት ግንዛቤ ያግኙ ስንል እንጋብዛለን።
በሰለሞን በቀለ
AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

All reactions:
5454