“መርዓዊ” ማለት በግዕዝ ሙሽራ ማለት ነው፡፡ መርዓዊ ስጦትም ለሥልሳ ዓመታት ገደማ ሙዚቃን ደግሞ ደጋግሞ ሲሞሽራት ኖሯል፡፡ አንድም ክላርኔት እየተጫወተ፣ አንድም እያቀናበረ፤ አንድም ዜማን በመከየን፣ አንድም ግጥም በመጻፍ ነው ሙዚቃን የሞሸራት፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ አብሪ ኮኮብ ሆኖ ብቅ ያለው መርዓዊ ለ55 ዓመታት ገደማ ክላርኔትና ሳክስፎን ተጫውቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙዚቃዎችን አቀናብሯል፡፡ እንዲሁም ተቆጥረው የማያልቁ ዜማና ግጥሞችን ደርሷል፡፡ በዘመናዊ ኪነ ጥበብ ውስጥ መቼም የማይደበዝዝ ቅርስ አኑሮ መርዓዊ ስጦት አርፏል፡፡ በዚህ ዓምድም የዚህን ታላቅ ሙዚቀኛ ሕይወትና ሥራዎቹን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡
በመዲናዋ የፈካው የአምባሰል አበባ
የክላርኔት ንጉስ በመባል የሚታወቀው መርዓዊ ስጦት ውልደቱና እድገቱ ወሎ አምባሰል ውስጥ ነው፡፡ ለመርዓዊ አምባሰል የበቀለባት አፈር ብቻ አይደለችም፡፡ አምባሰል በሙዚቃ ዘመኑ በክላርኔትና ሳክስፎን የኳላት ውብ ኪናዊ መገለጫውም ነች፡፡ ከአምባሰል የበቀለው ይሄ አበባ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መስክ ላይ ለዓመታት አብቦ ፈክቷል፡፡
የሙዚቃ ተመራማሪ ማዕረግ ጌታቸው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ታሪክ በከተበበት “ጠመንጃና ሙዚቃ” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው፣ መስከረም 25 ቀን 1928 በወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል ወረዳ ልዩ ስሟ ዲቃ የተወለደው የጥበብ አበባ ትምህርት ወዳድ በሆኑ ቤተሰቦቹ ግፊት ወደ ደሴ የተላከው ገና በለጋነቱ ነበር፡፡ ስመ ገናናዋ ደሴ ግን አስተምሪው የተባለችውን ሕጻን ገና በልጅነት ዕድሜው ለሙዚቃ አሳልፋ ሰጠችው፡፡ 1941 ዓ.ም በዘመኑ ተወዳጅ የነበሩት “ቴዎድሮስ” እና “ጎንደሬው ገብረማርያም” ተውኔቶችን ለከተማው ሕዝብ ለማሳየት ደሴን የረገጡት የማዘጋጃ ቴአትር ተዋንያን የተመልካቹን ቁጥር ለማብዛት በሚል የፋንፋር (የማርሽ) የሙዚቃ ትርዒትን በጎዳናዎች እያሳዩ ነበር፡፡
መርዓዊ ከቴአትሩ ይልቅ የቴአትር ማጀቢያ ሙዚቃው አስገርሞታል፡፡ ተፈራ አቡነወልድ የተባለው ሙዚቀኛ የሚጫወተው መሣሪያም ቀልቡን ገዝቶታል፡፡ የመድረክ ድግሱ እንዳለቀ ትንሹ ልጅ ወደ ሁለት ሰዎች ዘንድ ጠጋ ብሎ የያዙትን የሙዚቃ መሣሪያ እንደእነሱ እንዲጫወት እንዲያደርጉት ተማጸናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የማዘጋጃ ቴአትር የኦርኬስትራ ኃላፊ ተስፋዬ ለማና የዘመናዊ ሙዚቃ መምህሩ ኃብተጊዮርጊስ ገመዳ ነበሩ፡፡
በወቅቱ በሀገሪቱ ሙዚቃ ውስጥ ተጠቃሽ የሆኑት ሁለቱ ግለሰቦች መልከ መልካሙን ሕፃን አይቻልም አላሉትም። ይልቁንስ “እስኪ ደስ ይበለው” በማለት የማይሆን መስሏቸው አንድ ቃል ገቡለት። አዲስ አበባ ስትመጣ እናስተምርሃለን አሉት፡፡ መርዓዊ ገና በ13 ዓመቱ ሙዚቃን ወዷልና በራዲዮ ብቻ ወደሚያውቃት የኢትዮጵያ መዲና ለመጓዝ ልቡ ሸፈተ፡፡ ጉዞውን ሊያግዙ የሚችሉ ዘዴዎችን ጭምር መዘየድ ጀመረ፡፡ “ወደ ግቤ ካደረሰችኝ” በሚል መላምት መርዓዊ በ1942 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል የሳለውን የእንቁጣጣሽ ሥዕል ይዞ ደሴ ከተማ ላይ ወደሚገኘው ከልዑል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ቤተሰቦች ደጃፍ ደረሰ፡፡ ሥዕሉን ሲያበረክት 50 ብር ተሰጠው፡፡
ይህቺን ብር ይዞ ከቤተሰቦቹ ጠፍቶ ሙዚቃን እናስተምርሃለን ያሉትን ሰዎች ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ በትሬንታ ኳትሮ የጭነት መኪና ጉዞ ጀመረ፡፡ በዚህ አኳኋን ነው መርዓዊ የሙዚቃ ፍቅሩን ለመወጣት አዲስ አበባ የደረሰው። ከዚያ በፊት የማያውቃትን አዲስ አበባ እየተደናገረም ቢሆን ለመልመድና ህልሙን በተግባር ለመኖር ጥረቱን ጀመረ፡፡ በዚህ ጉዞ በጣም ፈታኝ የሆኑ የህይወት ውጣ ውረዶችን አሳለፈ፡፡ የኋላ ኋላ ግን ደሴ ላይ ሙዚቃ ያቀረቡትን ሰዎች አፈላልጎ አገኛቸው፡፡ የገቡለትን ቃል አስታውሶ ሲያናግራቸው፣ እነሱም ቃላቸውን አላጠፉበትም፡፡ መጠነኛ ድጎማ እየተደረገለት ሙዚቃን እንዲማር ተፈቀደለት፡፡
የሙዚቃ ታሪክ ተመራማሪው ማዕረግ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው፣ መርዓዊ ስጦት ልቡ ለክላርኔትና ሳክስፎን አብዝቶ የተሳበ ቢሆንም የመድረክ ሀ ሁን የለመደው ግን በቴአትር ነው። 1943 ዓ.ም ሴቶች የተውኔት መድረክ ላይ ደፍረው መውጣት ያልጀመሩበት ወቅት ነበርና መልከ መልካሙ መርዓዊ ስጦት “ንግስተ ሳባ” እና “ድንገተኛ ጥሪ” በተሰኙ ተውኔቶች ላይ የሴት ገጸ-ባሕርይን ተላብሶ እንዲጫወት ተደረገ፡፡ ትንሹ ልጅ የምኞቱን መኖር የጀመረው ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንግስና የብር ኢዮቤልዩ በዓል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በ1948 ዓ.ም ሲመረቅ ነው፡፡
በነገራችን ላይ መርዓዊ ከማዘጋጃ ቴአትር ተመርጠው ወደ ዘመናዊው የጥበብ ቤት ከተሸኙት ከያኒያን አንዱ ነበር፡፡ ትንሹ ልጅ አስቀድሞም በማዘጋጃ የሙዚቃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ አዳጊዎች አንደኛ ሆኖ ለሽልማት መብቃቱ ቢታወቅም ክላርኔትና ሳክስፎኑ ጎልተው የደመቁት ግን በአዲሱ የጥበብ ቤት ነበር፡፡ መርዓዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት ሲገባ ሙዚቀኛ ብቻ ሳይሆን የግጥምና ዜማ ደራሲ መሆኑም ተገለጠ። የአምባሰሉ አበባ ከዚህ ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ ሙዚቃ መድረክ ላይ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እንደ ኮኮብ የሚያበራ ፈርጥ ለመሆን በቃ፡፡
የሙዚቀኛው የጥበብ አበርክቶ
የሙዚቃ ተመራማሪ የሆነችው ትምክህት ተፈራ (ዶ/ር) ስለ መርዓዊ የሙዚቃ አበርክቶን አስመልክታ እንዲህ ትላለች፤ “ጋሽ መርዓዊ ከሙዚቀኛም በላይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ተወዳጅ ሙዚቃዎች ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የእርሱ አስተዋጽኦ በጣም ትልቅ ነው። ለብዙ አስርት ዓመታት የዘለቀው የሙዚቃ ሥራዎቹና አበርክቶው መቼም የማይደበዝዝ አሻራውን ትቶልን ሄዷል” ስትል አስተዋጽኦውን አስታውሳለች፡፡
ምንም እንኳን በመደበኛነት ከመድረክ ጡረታ ቢወጣም ለሙዚቃ ያለው ፍቅር ግን አልቀዘቀዘም ነበር የምትለው የሙዚቃ ተመራማሪዋ፣ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ የኪነ ጥበብ ቤቱ ከሆነችው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ቀጥሏል። የቴአትር ቤቱን በመጎብኘት ለሙዚቃ የሚያሳየውን ትጋት፣ ወጣት አርቲስቶችን በማስተማር እና የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንዲያድግ በማድረግ ረገድ እጅግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አርዓያ አድርጎ የሚያየውን የመርዓዊ ስጦት ህልፈትን ተከትሎ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባጋራው የሕይወት ታሪክ ላይ እንደገለጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የዘመናዊ ሙዚቃ ክፍልን በኃላፊነት መርቷል፡፡ በሙያው በግንባር ቀደምትነት ግንባር ድረስ በመሰለፍ ሀገር ወዳድነቱን አስመስክሯል፡፡ በሥራው እጅግ ታታሪና መልካም ስነ ምግባር የተላበሰ እንዲሁም ለሌሎች አርአያ የሆነ ታላቅ ባለሙያ ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በደማቅ ሁኔታ ሲከበር፤ የሙዚቃ ዝግጅት ቡድን፣ የትዕይንተ ጥበባት፣ የቅስቀሳ ዝግጅት አስተባባሪ ሆኖ ሰርቷል፡፡
ከሙዚቃ ሙያው በተጨማሪ የዘመናዊ ኦርኬስትራ ኃላፊ፤ የውዝዋዜ ክፍል ሀላፊ በመሆን በመሪነት አገልግሏል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው አርቲስት መርዓዊ ስጦት የተዋጣለት የግጥማና ዜማ ደራሲ፤ እንዲሁም አቀናባሪም ነበር፡፡ ለአርቲስት ምኒልክ ወስናቸው፣ ለመልካሙ ተበጀ፣ ለጠለላ ከበደ፣ ለፍቅርተ ደሳለኝ እና ለሌሎች አርቲስቶች ግጥምና ዜማ ደርሷል። በርካታ ሙዚቃዎችን አቀናብሯል። አንጋፋው አርቲስት መርዓዊ ሙዚቃ በማቀናበር ረገድ የምኒልክ ወስናቸው “የእንጆሪ ፍሬ”፣ “ትዝታ አያረጅም”፣ “ስኳር ስኳር”፣ “አፈር አትንፈጊኝ”፣ “በምድረ ሱዳን ያለሽው”፣ “ጥቁሯ ጽጌረዳ”፤ ለመልካሙ ተበጀ ደግሞ “ብዕር ብዕር”፣ “ሰላም ጤና ይስጥልኝ”፣ “ንቢቱ”፣ እንዲሁም የአርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ “ልማት ልማት” እና ሌሎችንም ሙዚቃዎች አቀናብሯል ።
ከዚህም ባሻገር ከ200 የማያንሱ አብዮታዊ መዝሙሮችን፣ ለሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እና ሌሎች በርካታ ታዋቂ ቴአትሮች ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ሰርቷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብም የመጀመርያ የሆነውን የክለቡን መዝሙር የሠራው አርቲስት መርዓዊ ስጦት ነው። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመን በተሰራው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ላይ የሙዚቀኛ መርዓዊ የትንፋሽ አሻራ ታትሞባቸዋል፡፡ ኦርኬስትራውን የመምራትና የማስተባበር ሥራንም በታላቅ ትጋትና ሥነ ምግባር በብቃት በመወጣት ታሪክ የማይዘነጋውን አስተዋጽኦ አድርጓል ሲል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ስለ ሙዚቀኛው የህይወት ታሪክ ላይ ባጋራው መረጃ አስፍሯል፡፡

የመርዓዊ ሽልማቶች እና ሥንብት
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባገኘነው መረጃ መሰረት የመላው ጥቁር ሕዝብ የሙዚቃ ፌስቲቫል (All Black People Music Festival) ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል፡፡ በናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሌሎችም ሀገራት በኪነ ጥበብ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል፡፡ የሙዚቃ ሥራዎቹንም አቅርቧል፡፡ አምባሰልና ትዝታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ በካሴትና በሲዲ በማስቀረጽ አሻራውን አስተላልፏል፡፡
መርዓዊ በሙዚቃውና የጥበብ ቤቶችን በመምራት ላበረከታቸው አስተዋጽኦዎች በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የማበረታቻና የመጽሐፍት ሽልማት፣ በደርግ ዘመን በማስታወቂያ ሚኒስትር የምስጉን ሰራተኛ ወርቅ ተሸላሚ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የወርቅ ሽልማት፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ማህበር የክብር ሽልማት፣ በቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (ባህል ማዕከል) የክብር ዋንጫ ተሸላሚ፣ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ጥቂቶቹ ናቸው።
“የክላርኔቱ ንጉስ” የሚል ቅጽል መጠሪያ እስከማግኘት የደረሰው መርዓዊ በተለይ በክላርኔት ልዩ የመጫወት ችሎታው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ እድገት ላይ ደማቅ አሻራውን ያሳረፈ ታላቅ የሀገር ባለውለታ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ከተወለደበት አምባሰል ርቆ አዲስ አበባ ላይ ቢከትምም በክላርኔት አምባሰልን ከሽኖ በአስደናቂ ሁኔታ በመጫወት በሙዚቃ መድረክ ላይ መንገስ ችሏል፡፡
አርቲስት መርዓዊ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በተወለደ በ89 ዓመቱ ከዚህች ዓለም ድካም አርፏል። አርቲስት መርዓዊ ስጦት የ 3 ወንድ እና 2 ሴቶች ልጆች አባት ሲሆን፤ የ6 ልጆች አያት የ1 ልጅ ቅድመ አያት እንደነበር የሕይወት ማህደሩ ያሳያል። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ ከቶም የማይዘነጋ ኪነ ጥበባዊ አበርክቶ በሰጠን ታላቁ ሙዚቀኛ መርዓዊ ስጦት ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡
በአብርሃም ገብሬ