ማህበረሰብን ያስቀደመው አገልጋይነት

You are currently viewing ማህበረሰብን ያስቀደመው አገልጋይነት

የረመዳን ወር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተለየ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ ወር ነው፡፡ ወሩ ፍቅር፣ መተዛዘን፣ መረዳዳት ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙም ፆሙን  ራሱን ለሀይማኖታዊ ስርዓቱ በማስገዛት፣ በጸሎትና በሰላት ከማሳለፍ ባሻገር የኢድ አልፈጥር በዓልንም በልዩ ሁኔታ ያከብረዋል፡፡ ቤተሰብ ከያለበት ተሰባስቦ፣ እየተበላና እየተጠጣ፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ፣ በደስታና በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡

በዚህ ሂደት ጤናን ሊያቃውሱ የሚችሉ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በዓል ላክብር ሳይሉ ለሙያቸው እና ላስተማረቻቸው ሀገራቸው የገቡትን ቃለ-መሃላ የሚፈጽሙ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ 

ወይዘሮ እመቤት ግርማ ይባላሉ፤ የኢድ አልፈጥር  በሚከበርበት አንድ የበዓል አጋጣሚ   የአስም ህመማቸው ይነሳባቸዋል ወደ ሀኪም ቤት መሄዳቸውን በማስታወስ፣ “በወቅቱ ሙስሊም ሀኪሞች ነበሩ ያከሙኝ፤ ጥሩ አገልግሎት ነው የሰጡኝ፡፡ በበዓል ቀን ገብተው ህዝቡን የሚያገለግሉ ሀኪሞች ክብር ይገባቸዋል፡፡ በዓልን ማክበር ሲኖርባቸው ጊዜያቸውን ሰውተው፤ ለእኛ አገልግሎት ለመስጠት በመገኘታቸው ልናመሰግናቸው ይገባል” ሲሉ ስላገኙት አገልግሎት ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ህመም በቀን መርጦ አይመጣምና እንደ ወይዘሮ እመቤት ሁሉ በበዓል ወቅት ህመም የሚያጋጥማቸው አሉ። ለእነዚህ ዜጎች አገልግሎት ለመስጠት በዓልን በስራ የሚያሳልፉ  ሀኪሞችም እንዲሁ፡፡ ከእነዚህ መካከል በአበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል የፅንስና ማህፀን ሀኪም ዶክተር አብዱልፈታህ አበበ አንዱ ናቸው፡፡ ዶክተር አብዱልፈታህ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ባለፈ በኢድ አልፈጥርና በሌሎችም በዓላት አዘውትረው ስራ ገበታቸው ላይ የመገኘት ልምድ እንዳላቸው ነው የገለፁልን፡፡  

እናቶች ለወሊድ፣ በደም መፍሰስ፣ ከማህፀን ውጭ እርግዝና፣ እጢና ለሌሎች ህመሞች ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ የሚናገሩት ዶክተሩ፣ እሳቸውም ብዙ ጊዜ በምጥና በቀዶ ህክምና የማዋለድ ስራ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው በመሆኑ በበዓል ወቅትም እነዚህን ተግባራት በመስራት ያሳልፋሉ፡፡ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም በቀን ከ10 እስከ 15 እናቶችን እንደሚያዋልዱም ነው የገለፁት፡፡

“በበዓል እለት እንዲሁም ከበዓል ውጪ ባሉ ቀናት አልፎ አልፎ ጠዋት ለስራ ስወጣ ቁርስ የማልበላበት ወቅት ይኖራል፡፡ ምሳ ሰዓት ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ከገባሁ በኋላ ደግሞ ስራዬን ሳልጨርስ መውጣት ስለሌለብኝ ምግብ ሳልበላ የዋልኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። የዛሬ ዓመት ደግሞ በረመዳን ፆም ወቅት ቀን 9 ሰዓት የቀዶ ህክምና ስራ ስለጀመርኩ ሰዓቱን ሳላውቀው ሳላፈጥር ከምሽቱ 4 ሰዓት ሆኗል፡፡ ቀዶ ህክምናውን እንደጨረስኩ አዞረኝ፡፡ ልወድቅ ነው ብዬ ለባልደረቦቼ ነገርኳቸው፡፡ እነሱም ተሯሩጠው የሚጠጣ ሰጡኝ፤ ይህ የማልረሳው ገጠመኜ ነው” ሲሉ ዶክተር አብዱልፈታህ ነግረውናል፡፡

“የህክምና ስራ የህሊና እርካታ የሚሰጥ ተግባር ነው፡፡ በበዓል ወቅት የህክምና አገልግሎት የሰጠናቸው ሁሌም ያስታውሱናል፡፡ ያገለገልናቸው እናቶች ታክመው፤ ልጆቻቸውን አቅፈው ሲወጡ ማየት ትልቁ ክፍያችን ነው፡፡ ሲያመሰግኑንም ለሌላ ስራ ያበረታታናል። ስለዚህ ማንኛውም የጤና ባለሙያ በበዓል ወቅት ገብቶ ቢሰራ የህሊና እርካታ ያገኛል፡፡ የሚጎዳው ነገር የለም” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

“እናቶች መቼ ምጥ እንደሚመጣባቸውና ድንገተኛ ህመም እንደሚከሰትባቸው አይታወቅም። በበዓልም ይሁን በማንኛውም ቀን ይከሰታል፡፡ እኔም ከሙያው ስነ ምግባር አንፃር በተፈለግሁ ሰዓት ቀንም ሆነ ማታ በማንኛውም ሰዓት በስራ ገበታዬ እገኛለሁ፡፡ ባለፉት የዒድ አልፈጥርና አረፋ በዓላት ገብቼ ቀዶ ጥገና አድርጌአለሁ፡፡ በየዓመቱ በበዓላት ቀን ድንገተኛ የቀዶ ህክምና ያጋጥመኛል። በዓል እያሳለፍኩ ተጠርቼም ሄጄ የምሰራበት ወቅትም አለ፡፡ ለመጪው የዒድ አልፈጥር በዓልም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ክፍል የእናቶችና ፅንስ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ሰይድ አራጌ ናቸው፡፡

በአጋጣሚ ደም መፍሰስ፣ ከማህፀን ውጪ እርግዝና ሲከሰት በድንገት የምጠራበት ጊዜ አለ፡፡ በዚህን ወቅት ለበአል ቤት እንኳን ብሆን ስራ ገብቼ ቀዶ ጥገና አድርጌ የምመለስበት ሁኔታ ያጋጥመኛል፡፡ ታማሚው ድንገተኛ ህመም አጋጥሞት ሊመጣ ስለሚችል ያን ህብረተሰብ አክሜ ሲመለስ ሳይ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ታካሚዎችም በበዓል ቀን ሄደን ስንሰራ በጣም ደስተኛ ይሆናሉ። ቤተሰቦቼም የምሰራውን ስራ ስለሚረዱኝ አመሰግናቸዋለሁ ብለዋል ዶ/ር ሰይድ፡፡

የህክምና ሙያ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት መሆን አለበት የሚሉት ዶ/ር ሰይድ፣ በማንኛውም ሰአት ህብረተሰቡን ስናገለግል ክፍያችን እርካታ በመሆኑ መስዋእትነት በመክፈል ማገልገል አለብን በማለት ዶ/ር ሰይድ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ሌላኛዋ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት በተጨማሪ በበዓልም አገልግሎት በመስጠት በስራ ማሳለፋቸውን የሚገልፁት በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተመላላሽ ህክምና ስራ ማመቻቸት ቡድን መሪ ሲስተር ቀቡላ ከድር ናቸው፡፡

“የኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት በአስተኝቶ ማከም ህመምተኞችን በመርዳት ያሳለፍኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህን በማድረጌ የህሊና እርካታ ይሰጠኛል፡፡ በበዓል ወቅት ቤቴ አለማክበሬ ብዙም አይሰማኝም፡፡ በወቅቱ ታማሚዎች ጋር አብሬ መዋሌና እነሱን በማገልገሌ ከምንም ነገር በላይ ደስተኛ ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም ህመምተኞችን መንከባከብና መርዳት ይጠበቅብናል፡፡ በእምነቱም እንዲህ አይነት ተግባር ማከናወን ትልቅ ዋጋ አለው” ይላሉ ሲስተር ቀቡላ፡፡

በበዓል ወቅት በስራ ቦታ ሆስፒታሉ ለህመምተኞችና ለሰራተኞች ምግብ ስለሚያዘጋጅ አንድ ላይ በመመገብ በዓሉን እንደሚያሳልፉ ነው የጠቆሙት። ሁሌም ደስተኛ ሁነን ህመምተኞችን መንከባከብና ማገልገል ይገባናል የሚሉት ሲስተር ቀቡላ፣ ለመላው ህዝበ ሙስሊም ለኢድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

በበዓል ወቅት ከናፈቁት ቤተሰብ፣ ከልጆች ጋር ማሳለፍ የሚሰጠውን ደስታ ወደ ጎን በመተው ቅድሚያ ለዜጎች ደህንነት በሚል፣ በየተሰማሩበት ዘርፍ ህዝብን በማገልገል ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ የሚያሳልፉት ባለውለታ የህክምና ባለሙያዎች ሊመሰገኑና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል። የእነዚህ ባለሙያዎች ያልተቋረጠ አገልግሎት በሁሉም ቀን አስፈላጊ ነው፡፡ ሌሎችም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ ህብረተሰባቸውን በቅንነት ቢያገለግሉ የህሊና እርካታን ብሎም በጎነትን ያተርፋሉ እያልን ለእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል ተመኘን፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review